289 116 953KB
Amharic Pages 117 Year 2022
መብቱ © ኤፍሬም ዳንኤል ኃይሌ ይህ መጽሐፍ በቅጂ መብት መብቱ በህግ የተጠበቀ ነው። በቅጂ መብት የተጠበቁ መብቶችን ሳይገድብ የዚህ እትም የትኛውም ክፍል ሊባዛ፥ ሊከማች አይችልም፥ ወይም ወደ መልሶ ማግኛ ሥርዓት ማስተዋወቅ፥ ወይም ማስተላለፍ፥ በማንኛውም መልኩ ወይም በማንኛውም መንገድ (ኤሌክትሮኒካዊ፥ ሜካኒካል፥ ፎቶኮፒ ፥ በቅጂ ወይም በሌላ መንገድ) ያለአሳታሚው ቅድሚያ የጽሑፍ ፈቃድ ማስራጨት የተከለከለ ነው። የመጀመሪያ እትም፥ 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ
ለአስተያየትዎ ኢሜል፦ [email protected] ፖ.ሳ.ቁ፦ 19933 አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ I made this eBook Free for mobile reading. If you love this book and feel like supporting the author 1000083243744 Commercial Bank of Ethiopia +251926720363 Ephrem Daniel Thank You!
ትዝክት የህይወትን ክራር ስመታው..... እስኪ አድምጡኝ አዝናኝ፥ አነቃቂ፥ አወያይ፥ ስሜት ቀስቃሽ ግለ-ጥቅሶች
ከ ኢ/ር ኤፍሬም ዳንኤል
2014 ዓ.ም አዲስ አበባ
መታሰቢያነቱ ለአባቴ ለዳንኤል ኃይሌ
ማስታዎሻነቱ ይሄንን ዓለም በየዘርፋቸዉ የተሻለ ለማረግ ለታተሩት፥ እየታተሩ ላሉት፥ እንዲሁም ወደፊት ለሚታትሩት ሁላ
ምስጋና ለመላዉ ቤተሰቦቼ፥ ወዳጅ ዘመዶቼ፥ ለጓደኞቼ፥ እንዲሁም ለእናንተ ለተከበራቹህ አንባቢያን በጠቅላላ ይሁንልኝ።
መግቢያ በፊት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ሙዚቃ እያቀናበርኩ በተለያየ ዓለም ለሚገኙት ደንበኞቼ በኢንትርኔት አማካኝነት ሙዚቃዎቼን እሸጥ ነበር። ሙዚቃ መስማት ብቻ ሳይሆን ማሰማትም ይመቸኝ ነበር። ቡኃላም እስኪ አሁን ደግሞ የህይወትን ክራር በስነጽሁፍ ድሃንጻ (ክሮቹን መምቻ መሳሪያ) ምታው የሚል ሃሳብ ጭንቅላቴ አቃጨለ። እነሆ ትንሽዋ ትዝክት ተወለደች። ውድ አንባቢያን፥ ይህን መጸሃፍ ስጽፍ እሩቡን እንኳን ሳልገፋ አንድ ማስተላለፍ ያለብኝ መልእክት እንዳለ ተሰማኝ። በዚህ መጻሃፍ ውስጥ የተካተቱት ምልከታዎች በተለያየ ጊዜያት ከአእምሮዬ ፈልቀው እኔም በብእርና በወረቀት ያሰፈርኳቸው ግለ-ፍልስፍናዎቼ ናቸው። ምንናልባት ከሌላ ነባር ሃሳብ ጋር የመመሳሰል አዝማሚያ ካላቸው በአጋጣሚ ሊሆን ይችላል። የመጸሃፉ ዕርእስ “ትዝክት” ከየት መጣ ላላቹህ፥ የትርክትና የትዝብት ቃላት ቁርኝትና ጥምረት የፈጠሩት ነው። ይህ መጸሃፍ መነበብ ያለበት እንደ ስድንባብ ሳይሆን፥ እረጋ ብላቹህ ከእያንዳንዱ አባባሎች ጋር እየተጫወታቹህና እየተዝናናቹህ ሲሆን ትግባባላቹህ። ቀስ ብላቹህ አጣጥሙት። እያንዳንዱ ጸሃፊ አንባቢው እንዲረዳለት የሚፈልገው ነጥብ አለ። ከዚህ ጥቅሳዊና ትዝብታዊ ይዘት ካለው ትርክት ቢያንስ አንድ ቁም ነገር ትቀስሙበታላቹህ የሚል ሙሉ ተስፋ አለኝ። መልካም ንባብ !
1
አሁንም ተማሪ ነኝ፤ የዲግሪው ምርቃት ትምህርቴን እንዳደናቀፈው ተረድቻለሁ። ለተወሰኑ ጊዜያትም ቢሆን አዋቂ አስመስሎኛል፥ እኔም ሳላቀው መስያለሁ። ትምህርቱን አልቃወምም፥ ምርቃቱን ግን አልደግፍም። ሰዎች ስለራሳቸው ያላቸው ግምት ከወረቀት ጋር ከተዛመደ፥ የውስጥ እምቅ ሃይላቸውን ሊያዳፍነው ይችላል የሚል እምነት አለኝ። አዋቂ ማለት ትክክለኛ ትርጉሙ ባይገባኝም፥ ተማሪ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ግን በየቀኑ ይበልጥ እያወኩት ነው።
ከፍተኛ መስዋዕትነትና ጀብዱ ለፈጸሙ የሃገራችን ጀግኖች ሃውልት ይቆምላቸዋል፥ ፈረስና አህዮቻችን መረሳታቸው ለምን?
ፍጥነት መቆጣጠሪያ የሚይዙ የትራፊክ ፓሊሶች የትራፊክ መብራትን ተክተው መስራት ይችላሉ፥ የመኪናውን ፍጥነት ባያቆሙትም ይቀንሱታል።
የውድድር ዓለም ውስጥ እየኖርን ሁሉም አሸናፊ ሊሆን አይችልም።
2
አንድ ልሙጥ ወረቀት፥ ገብቶልህ አምስት ብር፥ ተሸኘህ አንተማ፥ በፍቅር በክብር፥ ነፍስ ይማር የድሮው፥ ወረቀቱ አንድ ብር።
ጥሩ መካሪ ጥሩ አጥፊም መሆን ይችላል። የምትጠብቀው ነገር አንተንም ይጠብቀሃል። መብራት ሃይል ማይሆነው መብራትሃይል ሲሆን ነው።
ተስፈ መቁረጥ እወዳለሁ፥ በተለይ አንገቱን። ወረኛ ስድብ ነው፥ ዝምተኛ አይደለም። ልክ ስትወልድ ወላጅ ትባላለህ፤ ማሳደግ ስትጀምር አባት ትባላለህ።
በክረምት መሃል የምትወጣዋን ያችን የጧት ጸሃይ፥ በበጋ ብትፈልጋት አታገኛትም።
3
ብርቅዬ እንስሳ እንጂ ብርቅዬ ሰው አላቅም። በውሻ የተነከሰን ሰው “የውሻ ቁስል ያርግልህ” ብለህ አታጽናናውም።
ኑሮ ተወዶ ሰውን አረከሰው። ከሃብታም ሰርቀህ ለድሃ መስጠት ምን ክፋት አለው?
ለድሃው ሳይሆን፥ ድሃ እንዳይኖር እንስራ። ሁላችንም በአንድ አምላክ ብናምን የተሻለ ዓለም እንፈጥራለን፦ በህግ አምላክ!
ሶሻሊዝም በሰነፎች ይከሽፋል፤ ካፒታሊዝም በስግብግቦች ይፈርሳል።
አምባገነንነት ሲዘንጥ ዲሞክራሲ ይወጣዋል። የሙስናውን ዋንጫ ኦዲተሩ በላው።
4
ከአላማችን የህዝብ ብዛት መጨመር ይልቅ የሙቀት መጠን መጨመር ይበልጥ ሊያሳስበን ይገባል።
ሳይንስ ሲጠግብ፥ ሃይማኖት ያገሳል። በዛሬዋ ዕለት ጓደኛህን ከአንድ ሳምንት ቡኋላ በአካል ልትጎበኘው ወስነሃል። እሱ ግን ዛሬ በህይወት የለም። በህይወት እንደሌለ የተረዳኽው፥ ከሳምንት ቡኋላ ልትጠይቀው በወሰንክበት ዕለት ስልክ ስትደውልለት ነው። ጓደኛህ ሳምንቱን ሙሉ በህይወት ነበር ማለት ይቻላል?
ጋሼ ማረኝ ማረኝ፣ ጋሼ ማረኝ ማረኝ፥ ዶሮ ሺ አወጠች እኔን ስጋ አማረኝ። (በድሮ ጊዜ ብር ተብሎ ተዘፍኖለት ነበር)
ገላግሌ የእንቅልፍ መድኃኒት፦ ሞት! የተቆላመጠን ስም ማቆለማመጥ ለመቀለማመጥ። የአንተ ወሰን የዓለምህ ወሰን ነው።
5
የሰው ልጅ ፍላጎት ጨዋማ የባሕር ውሃ እንደመጠጣት ነው፤ በጣም ስትጠጣ በጣም ይጠማሃል።
እንደ ድብርት የሚያም ነገር የለም። እራሴን መውደድ ሳልችል ስቀር፥ እጣላዋለሁ። ለፍጡራን ያለህ ከበሬታ፥ የአንተ ማንነት መገለጫ ነው።
ሺ አመት ላይኖር የሚሊየን አመት ጥላቻና ቂምበቀል ይቅር።
“ዛሬ ከእኔ ጋር ትሆናለህ!” ይህን ያአምላክህን ጥሪ እንደምትናፍቀው ሁላ እጅግ ትፈራዋለህ።
ሁሉም ጀግና ሰማዕት ነው፥ ሁሉም ሰማዕት ግን ጀግና አይደለም።
6
በቀላሉ ተስፈ የሚቆርጥ ሰው በቀላሉ ሎተሪ ይቆርጣል።
ኢኮኖሚው ሲዳከም የፖለቲካው አፍ ይሾላል። እስካላየሁህ ድረስ አልተፈጠርክም! ሃሳብ የህሊና ባሪያ ነው። በእንቅልፍ ሰዓት ሰው እና እንስሳት አንድ ይሆናሉ። “ዛፉን በፋስ መጥረቢያ ስሩን ብሎ ጣለው” አለ አንዱ የዓይን እማኝ የዕጽዋት መብት ተሟጋች፥ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ።
ድሮ
1 ብር + 1 ብር = 100 ብር፤
ዘንድሮ 100 ብር + 100 ብር = 1 ብር። (የሂሳብ ቀመር ስሌት እንደየጊዜው መከለስ አለበት!)
የስንኩል ስንኩል፥ ሃሳበስንኩል!
7
“ያለው ይጨመርለታል” የሚለው ሃይማኖታዊ አባባል ካፒታሊዝማዊ ይዘት አለው። ሶሻሊዝም ሃይማኖታዊ ይዘት አለው።
እቃህን ለመግዛት ምርጡ ቀን ዛሬ ነው፤ ነገ እቃው ገንዘብህን ይገዛዋል።
ፖለቲካ ውስጥ የምንም እጥረት የለም፥ በተለይ የምላስ።
ፖለቲከኛው ኢኮኖሚስቱን ሲያሳልመው አይቶ ጠበቃው የህግ መወሰኛ ምክርቤቱን ባረከው።
የዋጋ ግሽበት ህገወጥ የታክስ መሰብሰቢያ ስርዓት ነው።
ኢኮኖሚስቱ ትንቢት ተናጋሪ፥ ፖለቲከኛው ትንቢት ሰባኪ፥ ህዝቤ ትንቢት ተንታኝ።
8
ዲሞክራሲ ሲያሰራ እንጂ ሲሰራ አላየሁም፥ አምባገነንነት ሲሰራ እንጂ ሲያሰራ አላየሁም።
በእውቀት ያበደ ጭንቅላት ፍሬው ጤናማ ነው። የህይወት እንቆቅልሽ በምን አውቅልሽ ተመልሷል። ህይወትን አክብደህ አትያት፥ ታቀልሃለች! ተቆጣጣሪ የሌላት ሃፍረት፥ ውርደት ትወልዳለች። ካወራህ አልሰማህም! ተናገርና ላድምጥህ። ህጻን ልጅ ማልቀሱን ሲያቆም ከረሜላ አትሸልመው። አልቅሶ ማቆም ከረሜላ ሚያሸልመው ይመስለዋል።
የዓለም መጨረሻ ነገ ነው ቢባል፥ የሰወች እውነተኛ ማንነት ዛሬ አደባባይ ይወጣል።
9
የባህታዊያን ኑሮ ሚስጥር ነው፤ ሞተህ ለመኖር እየኖርክ መሞትን መምረጥ!
መፈጠር የሌለባቸው ሰዎች ሰውን ሲያጠፉ ሳይሆን ሰውን ሲፈጥሩ ማየት ይበልጥ ያቆስለኛል።
በህልሜ ህልም አየሁ፤ ለመንቃት ሁለቴ መነሳት ነበረብኝ።
በዚህ ዓለም የተሰጠኝ ገጸባህሪ አስቸጋሪ ነው። መርማሪ ሳይሆን ተመርማሪ መሆን እፈልጋለሁ፤ አሁንስ እኔንም አሞኛል!
እጆቻቸውን በጦርነት ላጡ ጀግኖቻችን ክብር ነው እንጂ፥ የሌባስ እጅ መቆረጥ ነበረበት።
ህይወት በዘፈቀደና በውስብስብ ነገሮች የተሳሰረች ክስተት ናት፤ እቆጣጠራታለሁ ማለት ዘበት ነው። አቅምህን እወቅ፥ ምትችለውን አድርግ፤ ከዛ ውጭ ችግሩ የአንተ አይደለም። በራስህ አትጸጸት፥ በራስህ አትዘን፥ በራስህ ግን እመን።
10
ሳያንኳኩ ሚከፈትላቸው እነሱ እድለኞች ናቸው። አንኳኩተው የሚከፈትላቸው እነሱ ታታሪዎች ናቸው። እያንኳኩ የማይከፈትላቸው እነሱ ብዙኃን ናቸው።
የፖለቲካ መሪዎች የስራ ዘመን፦ አንደበተርቱዕ > መሪ ... ለፍላፊ > አስተዳዳሪ ... ውሸታም > ቀጣፊ። (ቀጣፊ፥ ትርጉሙ እንደ አገባቡ ይለያል!)
እኛ ኢትዮጵያዊያን ቻይ ህዝብ ነን፤ አህያ ግን አይደለንም።
ቅዥት ባይኖር ህይወት ደባሪ ትሆን ነበር፤ አንዳንዴ ከእውነታው ማምለጥ ያስፈልጋል።
እራሱን በፍጹም በመስትዋትም ሆነ በካሜራ አይቶት የማያቅ ሰው እራሱን እንዴት አድርጎ ይስለው ይሆን?
11
የሰዎች ውሳኔ በእውነተኛ ፍላጎታቸው ላይ መሠረት ያደረገ ሳይሆን እንደ ወቅታዊው ሁኔታና አመላቸው ተለዋዋጭ ነው።
አጠቃላይ እውቀት ለወሬ ያመቻል፤ ጥልቅ የሆነ እውቀት ለስራ ያመቻል።
ጨለማ የብርሃን አለመኖር እንጂ ጥቁረት ባህሪው አይደለም።
እመን እንጂ ውኃውም ወይን ነው። ከምቾትህ ክልል ስትወጣ የሚሰማህ ስሜት፥ ውስጥ ሆነህ ከሚሰማህ የላቀና የገዘፈ ነው። በጎም ይሁን መጥፎ አዕምሮህ ውስጥ ሚቀረው እሱ ነው። አዲስ ተሞክሮ፥ አዲስ ምልከታ፥ አዲስ ህይወት!
በሓሪህን እንደ ልብስ ልለዋውጥህ ብትለው፥ “ጸባይህ መስልኩህ እንዴ?” ይልሃል።
12
ሁላችንም የዚህ ዓለም እስረኞች ነን፥ ነጻነታችንን የምናውጅበት መንገድ ግን ስለ ማንነታችን ብዙ ይናገራል።
የሰዎችን ባህሪ በቀላሉ መረዳት፣ ማብራራትና መተንበይ ከፈለክ፥ መጀመሪያ ከራስህ ጀምር።
የጸብ መነሻ ከነዚህ ሊያልፍ አይችልም፦ ወይ በገንዘብ፥ ወይ በስልጣን፥ ወይ በሴት፥ ወይም በጉራ ነው።
መርጠህ ከመጸጸት የተሰጠህን ተቀብለህ ማጉረምረም ይሻላል።
እድሜ ለቃላት፥ ሃሳብን ነጻ አወጡት። የሃሳብ ነጻነት በቃላት ተረጋግጧል!
ቤትህ ግድግዳ ላይ በፍሬም የተሰቀለ የሰው ምስል ካለ የአምልኮ ተከታይ ነህ።
13
ተቀብሎ የማይሰጥ ሰው ስግብግብና ደነዝ ነው፤ ድንጋይ እንኳን ያነጠርክበትን ኳስ መልሶ ይሰጠሃል።
ስትሰክን የምታየውን ነገር እንደ ብርሃን ብትፈጥን አታስተውለውም።
ሚዲያ ስድስተኛው እና ዋነኛው የስሜት ህዋሳችን ነው።
ለጉረኛ ሰው እዘንለት፥ ከራሱ ጋር አይደለም። ባህሪህን እመነው፥ አንድ ነው። ጸባይህን ተጠራጠረው፥ ተለዋዋጭ ነው።
ብዙ አትጠጣ፥ ገንዘብ ስትጠይቅ “ዥርዥር ሽጠኝ” ያስብልሃል።
እንደነ ውሮ ውርርር፥ እንደነ ኩኩም ኩኩሉ ብለህ ስያሜህን እራስህ አስወስን፤ የሰጡህን ስም ዝም ብለህ አትቀበል።
14
“እገሌ እኮ ከዚህ ዓለም አለፈ” አለኝ። ለፈተናው በደንብ ተዘጋጅቶ ነበር ማለት ነው!
ሰዎች ያላቸውን የእምቅ ሃይል ጥግ ለማወቅ ከፈለክ ሃላፊነትን ለየብቻ ስጣቸው፤ በቡድን ሚሠራ ስራ ለሰበብአስባብ እና ለማልገጥ የተጋለጠ ነው።
ሱስ ማለት ማምለጥ የማንችለውን ተፈጥሯዊውን የህይወት እስርቤት ማስረሻ፥ ብሎም እራሳችን የምንገነባው ሰውሰራሽ እስርቤት ነው። እኛ እንጀምረዋለን፥ እሱ ይጨርሰናል።
ራሱን መከላከል የማይችል ሰው ለመከልከል ብቁ አይደለም።
ትውስታ ባይኖር ቂም በቀል አይኖርም። አሁን ከህይወት ጋር ጦርነት ፈለገ፥ ቀኑ ደርሶ ለሞት እጅ ለሚሰጠው ነገ።
15
ሰበብ፥ በራስ መተማመን እንዳይጎዳ የሚጠባበቅ ሽፋን ነው።
በየሰፈሩ የሚታየው የወንድ ውሾች የእርስ በእርስ ፍቅር በእኛም ላይ እንዳይዛመት!
በእጣፋንታ ለሚያምኑ ሰወች ተስፈ መቁረጥ ብርቅ አይደለም።
ነቅቻለሁ? አላወኩም። ግን አሁንም መቀስቀስ እፈልጋለሁ!
አንዳንድ የሴትና የወንድ መጠሪያ ስሞች ስለተፈጥሯዊ ማንነታችን የሚነግሩን ነገር አለ። ሰላም - አሸብር ትህትና - ኩራባቸው ትዕግስት - በላቸው የወርቅውኃ - እሳቱ ዉሮ - አውራሪስ።
16
ሁሉም ተበዳይ! ግን ማንነው በዳይ? እያለቀስኩ እንዳልመጣሁ እየሳኩኝ እሄዳለሁ! በሲዖል እንድታምን የሚያደርጉህን ሰዎች ከህይወትህ ሰርዛቸው።
አንጀባ የበታችነት ስሜት ሚዛን መጠበቂያ መሳሪያ ነው።
ከጦርነት ሁላ አስከፊው ጦርነት ከራሳችን ጋር የምንፈለመው ነው።
ጠጥቶ መንዳት የመኪና አደጋ አያመጣም! እንደውም 8 ብርጭቆ ውሃ በየቀኑ ጠጣ።
እየተወደደ ሲመጣ ሚጠላ ነገር ኑሮ ብቻ ነው። ለሟቾች ቁጥር መጨመር የቀብር አስፈጻሚዎች ጸሎት ምክንያት ሊሆን አይችልም።
17
የማለዳዋ ታታሪ ወፍ ብዙ ትላትል ትለቃቅማለች። ለታታሪዎቹ የጧት ትላትሎች ግን ይህ ጥሩ ዜና አይደለም።
በጣም ትዕግስተኛ ሰው በጊዜ የሚቀልድ ይመስለኛል፤ መቶ ሜትር በእግር ለመጓዝ መቶ አመት ሊፈጅብህ አይገባም።
አንድ ቀን ለአንድ ስዓት ብቻ የሚቆይ የመሰወር ችሎታ ተሰጠህ። ማንም ሰው በዛች አንድ ሰዓት ምን እንዳደረክ አያቅብህም። ምን ታደርጋለህ? ለመልሱ አንድ ደቂቃ ተሰቶሃል።
ከላይ ለተቀመጠው ጥያቄ በሰጠኸው መልስ መሰረት፥ ስነምግባር የተላበስኩ ሰው ነኝ ካልክ፥ ጥሩ ዜጋ ነህ።
አንድ ሰሞን ክርክር ብለህ የፈረጅካቸው ንግግሮች መልካቸው ወደ ንትርክ ከተለወጠብህ፥ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ተራምደሃል ማለት ነው።
ባትረዳኝም እረድሃለሁ።
18
ጥሩ አንባቢ ሳትሆን ጥሩ ጸሃፊ እንደማይወጣህ ሁላ፥ ጥሩ አድማጭ ሳትሆን ጥሩ ተናጋሪ አይወጣህም።
በአንድ የእንግሊዝኛ ቃል የሚገለጽ አንድ ሃሳብ፥ በአራት በአምስት የአማርኛ ቃል ላይገለጽ ይችላል።
ሲናደዱ እቃ ሚሰብሩ ሰዎች ተሰባሪ ናቸው። ሰወች በውስጣቸው የሚያስቡትን ነገር የማወቅ ችሎታ ቢሰጥህ፥ ከአንድ ሳምንት ቡኋላ ራስህን ታጠፋለህ።
አንድ ሚሊየን ገጾች ያለው መጸሃፍ በከባድ መኪና ተጭኖ ሲያልፍ እንደምንም ብዬ እርዕሱን አነበብኩት። “ሴቶችን የማወቅ ሚስጥር”
መቶ ብር ያበደርከው ሰው ከጠፋብህ፥ ምናልባት ሌላ ሰው በሁለት መቶ ብር ሰውዬውን ገዝቶት ይሆናል።
19
እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች “አንተ እያልኩ ላውራ ወይስ አንቱ” የሚባል ቋንቋ አያቁም።
የዩኒቨርሲቲ መጸዳጃ ቤት ግድግዳ ላይ አንድ ማስታወቂያ ከፍ ብሎ ይነበባል፦ “ከዚህ መስመር በላይ አሳልፈህ ከሸናህ እሳት አደጋ ይቀጥርሃል።”
“ከንቱ ህይወት” ... በፍጹም መቀበል የሚከብድ ሃሳብ!
ዝግመታዊ፥ ጥንቁቅ፥ አሰልቺ = ደባሪ! ቀልጣፋ፥ ግዴለሽ፥ ደማቅ = ህይወታዊ!
አነቃቂ? ተነቅናቂ? ተነቃናቂ? የትኛው ነህ? የሰው ልጅ 99 በመቶ እንስሳ ነው፥ 1 በመቶው ግን እንስሳ አላስመሰለውም። 1 በመቶው እንስሳ ያላስመሰለው እንስሳ = ሰው!
20
አማርኛ ፦ አንተ፥ አንቺ፥ እናትተ፥ እርስዎ እንግሊዝኛ ፦ ዩ (You)!
በትዝታ ያሸበረቀች ህይወት ብልጭታዋ ብቸኝነትን ያባራል።
ማንበብ ሙሉ ሰው ያደረጋል፥ እውነት ነው። መሙላት ያለበት ግን ያንተ ብርጭቆ ሳይሆን አጠገብህ ያለው ባዶ በርሜል ነው።
ከራሱ ጋር ጦርነት ገጥሞ ራሱን ያሸነፈ፥ ከሌላው ጋር አይጣላም።
አንድ ሰው ብቻ ነኝ ብለህ አታስብ፥ ብዙ ሰው ነህ። ፍላጎትህ ለዛ ነው የበዛው።
የ50 ብር እቃ 100 ብር ገዛሁ፤ ሞቅታው 50 ብር አስከፍሎኛል።
21
እራሳቸውን የሚያጠፉ ሰወች ጉረኞች ናቸው፥ እንደ አጼ ቴዎድሮስ ለመሆን ነው? እጅ ላለመስጠት?
በጎች ለሰው ልጅ ምግብ ሁኑ ተብለው ተፈጥረዋል። ለመበላት መኖር ምን ይመስል ይሆን?
ወሰን የለሹ የሰው ልጅ ፍላጎትና የማይጨበጠው የህይወት እንቆቅልሽ በምሳሌ፦ ሐ = ሀመሩሐ ሐ ፊደል ሲያጋጥምህ ሀመሩሐ እያልክ አንብብ። አሁን “ሀመሩሐ”ን አንብበው። ሀመሩ ሀመሩ ሀመሩ ... ሐሐሐ
ጥይት ጠጥተው የሞቱ ሰዎች አሉ፥ አንተ ብትጠጣ ግን አትሞትም። እርግጠኛ ሆኜ እወራረዳለሁ! አንተ ብቻ በውሃ ማወራረድህን እርግጠኛ ሁንልኝ።
22
በአለማችን ከ3,000 በላይ ሃይማኖቶች አሉ። አንተ የተወለድከው አሁን ካለህ ሃይማኖት የተለየ ሃይማኖት ተከታይ መሐበረሰብ ውስጥ ቢሆን፥ አሁን ያለህን ሃይማኖት ምታገኘው ይመስለሃል?
የወረቀቱ የ100 ብር ኖት ወደ ሳንቲም መለወጥ አለበት!
99.9% የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የሌሎቹን ስም ያጠላሻሉ!
እንደ በሬ ነጂ ከኋላ ሆነው ይመሩናል/ይነዱናል፤ አንዳንዴም በአለንጋ እየገረፉ።
አማርኛ ቋንቋ ከ450 በላይ ፊደላት አሉት፥ ሃብታም ነው፤ እንግሊዝኛ 26 ብቻ። በቃላት ብዛት ግን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ከአለማችን እጅግ የናጠጠ ባለጸጋ ነው።
23
አንድ ቀን ሬድዮ እየሰማሁ አንድ ጋዜጠኛ “የእንትኑ እንትን” ሲል ሰማሁት። ሰምቼ የማላውቀው አዲስ ቃል ተማርኩ።
የ5 ሊትር ዘይት ገዝተው ወደ ቤት የሚገቡ ሰወች የፖሊስ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል!
ኢፍጹማዊ ዓለም ውስጥ እየኖርክ ፍጹማዊነትን መጠበቅ የስንፍና ምልክት ነው።
ሁሉንም ነገር መሆን መፈለግ አንዱንም ነገር መሆን አለመፈለግ ነው።
አስገራሚዎቹ የአማርኛ ሐረጎች፦ -
So እእእ ስለዚህ ...
-
I mean እእእ ማለቴ ...
-
Like እእእ እንደ ...
-
I don’t know ... ማለት
-
ይሄ ምንድነው ሚባለው ... እእእ ... እንትን
24
ጸባይህ ባህሪህን ከመሰለ፥ ፈታ ያልክ ሰው ነህ። ባህሪህ ጸባይህን ከመሰለ፥ ምትጨናነቅ ሰው ነህ። ጸባይህ ባህሪህን ከሆነ፥ ግዴለሽ ሰው ነህ። ባህሪህ ጸባይህን ከሆነ፥ አስመሳይ ሰው ነህ።
ጉረኛ ስው አለኝ የሚልህን በ10 ብታካፍለው ያለውን ማወቅ ትችላለህ።
Advertisment – እዩኝ እዩኝ ነው። Marketing - እወቁኝ እወቁኝ ነው። Sales - ግዙኝ ግዙኝ ነው። Political Campaign - ስጡኝ ስጡኝ ነው።
የቤት ኪራይ የክፍያ ቀን ማለት ተከራይ በቤት እንስሳት የሚቀናበት ቀን ማለት ነው።
ጸባይህን ስዎች ይንገሩህ እንጂ አንተ አትንገራቸው፥ ባሪያ ያደርግሃል።
25
በአለማችን ጠንካራው ነገር አልማዝ ነው ይላሉ፤ እኔ እምነት ነው ባይ ነኝ። እምነት ካለህ አልማዙን ትሰብረዋለህ።
የመብራት በተከታታይ ብልጭ ድርግምታ በገና የበዓል ቀን ብቻ ቢገደብልን?!
በአለማችን ብቸኛ የማይለወጥ ነገር ቢኖር ለውጥ ነው።
መንግስት ራሱ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው። አቶ ዝናቡ ሲመጡ አቶ መብራቱ ይጠፋሉ። የስኬት መገኛ ከፍርሃት በስተጀርባ ነው። እያንዳንዱን ቀን እንደ መጨረሻው የሚኖር ሰው እንደ አዲስ ከሚጀምረው በተሻለ ይኖራል።
አንዳንድ የታክሲ ሰልፎች ከመርዘማቸው የተነሳ እራሳቸው ታክሲ ያስፈልጋቸዋል።
26
ስለትኩረት ኃያልነት ማወቅ ከፈለክ፥ ከአንድ ስዓት ቡኋላ ስቅላት የሚጠብቀውን እስረኛ ጠይቀው፥ ጊዜ ካለው ይነግረሃል።
“ለካስ ይሄም አለ?” እያልክ ራስህን የምታጽናና ስው ከሆንክ “ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል” እያልክ ጉድጓድ ትገባለህ።
በነገሮች አትማረር፥ አትዘን፥ አትጸጸት የሚሉ ምክሮች አይገቡኝም፤ ታዲያ ምኑ ላይ ነው መንፈሳዊነታችን?
ብዙ ነገሮችን እንፈልጋለን፥ እራሳችንን አንፈልግም፤ ብዙ ነገሮችን መሆን እንፈልጋለን፥ እራሳችንን መሆን አንፈልግም፤ እራስህን ፈልግ፥ እራስህን ሁን፤ እራስህን ውደድ፥ እራስህን ኑር።
ቅድመ አያቶቻችን እንደኛ ባይመቻቸውም ከእኛ የተሻለ ተደስተው ያለፉ ይመስለኛል።
27
ትችት ወደፊትም ወደኋላም አነበብከው ያው ነው፥ አይቀርልህም። አንዱን “ት” አጥፋውና “ትች” በለው።
እንደ ጀ ጀነን፥ እንደ ፈ ፈንደድ፥ እንደ ዠ ዠርገግ፥ እንደ ጨ ጨበጥ፥ እንደ ቀ ቀበጥበጥ፥ እንደ ጠ ጠበቅ፥ እንደ ሸ ሸንቀጥቀጥ፥ እንደ ወ ወዝወዝወዝ፥ እንደ ዘ ዘነጥትጥ።
አብዛኛው ጊዜ ስኬት ሳታውቀው ትይዝሃለች፤ አውቄ ልያዝሽ ስትል፥ ታለፋሃለች።
በድብርት ብዙ ወራትን አሳለፍኩ። አሁን ግን ቆረጥኩ። አንድ ቀን በቀላሉ የማይበጠስ ጠንካራ ገመድ ከሱቅ ገዛሁ። በነጋታው ጧት ተነስቼ ማንም ዝር የማይልበት በዛፍ የተጠቀጠቀ ጫካ ውስጥ ገባሁ። አንድ ብዬ ዝላይ ጀመርኩ።
ለመኖር መብላት ሰዋዊ ነው፥ ለመብላት መኖር እንስሳዊ ነው።
28
በቃኝን ሳታውቅ እርካታን አትመኝ። የደስታው ቁልፍ ካዝናው ላይ ተንጠልጥሏል። ራሴን በእራሴ አሸንፌዋለሁ፥ የአንተ ፈተና ይለፈኝ። የሰው ማግኔት መሆን አልፈልግም። ሰው መሰሉን ያቀርባል ተቃራኒውን ያርቃል፤ ማግኔት መሰሉን ያርቃል ተቃራኒውን ያቀርባል።
የውሻ መንጋ ጎራ ለይቶ ሲናከስ ሳይ፥ የድሮ የሰፈራችን ጥል ትዝ ይለኛል።
“ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባበትም”፥ ለተራ ነገር ያዋጣል። “ከመናገር ደጅ አዝማችነት ይቀራል”፥ ለቁምነገር ያዋጣል።
በአስቸጋሪና አስከፊ ጊዜ የሰው ልጅ ለጸሎት ወይም ለባእድ አምልኮ ያለው ፍላጎት ይጨምራል።
29
ለሚቀጥለው ጥያቄ መልስህ “አው” ከሆነ ስራህን ትወደዋለህ። ያለ ደሞዝ ትሰራዋለህ?
የሰወች ጥንካሬ የሚያጠነክርህ ከሆንክ ገፊ ነህ። የሰወች ድክመት የሚያጠነክርህ ከሆነ ጎታች ነህ።
ሰማይ ሲደምን ደስ ይላል፤ ጫጫታን አጥፍቶ እርጋታን ያመጣል።
ራስህን በደንብ ጠበክ፥ አካላዊ እንቅስቃሴ አደረክ፥ የተመጣጠነ ምግብ በላህ ጠጣህ፥ ነገ ቀንህ ደርሶ ጠፈህ። ለዚሁ ነው?
እምነት ወደ ተስፈ የምታደረገው ግስጋሴ፥ ተስፈ መቁረጥ፤ ተስፈ ወደ እምነት የምታደረገው ግስጋሴ፥ ኃይማኖት።
30
በእዚህ ዓለም እያንዳንዱ ነገር ፍጹም ተቃራኒ የሆነ መንትያ አለው፥ ለብርሃን ጨለማ፥ ለፍቅር ጥላቻ፥ ለለጋስ ስግብግብ፥ ለህይወት በድን፥ ለበጎ መጥፎ፥ ለደስታ ሃዘን፥ ለሰላም ጦርነት፥ እያለ ይቀጥላል።
እድሜህ እየገሰገሰ መሆኑ የሚሰማህ የልጅነት ትዝታ ፊትህ ሲደቀን ነው።
መሪ ፊት ለፊት ሆኖ ይመራል፥ ለዚህም ነው መሪ የተባለው። ከኋላ ሆነህ የምትመራው ከብትን እንጂ የኢትዮጲያን ህዝብ አይደለም።
ገንዘቡን አባረኽው፥ ገንዘቡን ደርሰህበት፥ ገንዘቡን መተኽው፥ ገንዘቡ የሚያሳድድህ ከሆንክ፥ አንተ ሃብታሙ ነህ።
31
ይመቸኛል ብለህ ከምታስበው ግን በእርግጥ ካልተመቸህ መንገድ አሁኑኑ ውጣ፤ ላይመቸኝ ይችላል ብለህ ከምታስበው መንገድ ተቀላቀል፥ ትማርበታለህ፥ ትማረክበታለህ። ከሁሉ በላይ ግን ራስህን በተለየ መስተዋት ታይበታለህ። እንደ በፊቱ አይደብርህም።
ስሜታዊነትን ሙሉ ለሙሉ ስትላበስ፥ ምክንያታዊነት ባዶ ራቁቷን ትቀራለች።
አንድ ወታደር ለደሞዝ ብሎ ህይወቱን የሚገብር አይመስለኝም። ከሆነ ግን፥ በሚያገኘው የደሞዝ ዋጋ መጠን ሃገሩን እየሸጠ መሆኑን ሊረዳው ይገባል።
ተስፈ በጥርጣሬ የተለወሰች እምነት ናት። በመከራ ውስጥ ያለች ደስታ ከሃሴት ትበልጣለች። የአዲስ አበባ መንገዶች ሲጸዱ፥ ነዋሪዎቿ ይቆሽሻሉ።
32
ፈረንጅ የዱር እንስሳትን ማደን ያዝናናዋል፥ አንዳንዴም እንደ ስፓርት ይታያል። እንስሳቶቹ ጠመንጃ ቢሰጣቸው ደግሞ ይበልጥ ጨዋታውን ያደምቀዋል።
በመፈጠርህ አትዘን፥ ምንም ማድረግ አትችልም፥ በመጨረሻ እኮ ትካሳለህ።
ከአንድ እረዥም እርምጃ፥ ትናንሽ አጫጭር እርምጃ መውስድ የተሻለ ነው። ከወደክ ብዙ አትጎዳም።
ለሚዛን ግራ የገባው ብቸኛ ነገር እድል ነው። ለመኖር እየኖርን መኖርን አንርሳ። አንድ መጽሃፍ ሙሉውን ከማንበብ ይልቅ፥ ከመጽሃፉ ጭብጥ የወጣ አንድ ጥቅስ በአእምሮ ማሰላሰል የላቀ ጥቅም አለው።
33
የስነ-አእምሮና የስነ-ልቦና ምሩቃን ዘርፉን የተቀላቀሉት፥ መጀመሪያ የራሳቸውን ችግር ከመፍታት መንፈስ ይመስላኛል።
መሪዎቻችን ይዋሻሉ የሚል እምነት የለኝም፥ እነሱን አድማጮች የሉም የሚል እምነት እንዳለኝ ሁላ።
በጉብዝናና በስንፍና መሃል ያለው ልዩነት፦ የመጀመሪያው የሚከፍልህ አቆይቶ ግን አብዝቶ፥ ሁለተኛው፥ በቶሎ ግን አሳንሶ።
ማወቅ ጭንቀትን ካመጣ፥ አለማወቅ ሃሴት ነው። እራስን መውቀሱ መልስ አይደለም፥ እራስን መፈረጁ መልስ አይደለም። አንተ ዳኛ ሳትሆን ለራስህ ተከራካሪ ነህ፥ መብትህን አስጠብቅ።
ሎተሪ፦ የስራፈቶች ተስፈ ዓለምላሚ የመንግስት ብጫቂ ወረቀት።
34
ሚስጥርን ከፈለከው ትርጉሙ ጠፍቶኃል ማለት ነው።
በጉጉት የተሞላች ነፍስ በፍጹም አትደበትም፥ ከተደበተች ግን እራሷን ታጠፋለች።
አንዳንድ ሰወች ከሚጨነቁልህ ይበልጥ እንዴት እንደሚጨነቁልህ ለማሳየት የሚያደረጉት ጥረት አንተን መልሶ ያስጨንቀሃል።
ተስፋም ሲንዛዛ ተስፋ ያስቆርጣል። የስው ልጅ በተፈጥሮው የዋህ ነው፦ መብላት፥ መጠጣት፥ መጫወት፥ መተኛት፥ ዘር መተካት፥ አለቀ። የተፈጥሮ አድሏዊነት ግን የዋህነቱን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይከተዋል።
ብዙ መንገድ መጓዝ የለብህም እመነኝ፥ አንዲት በሳል ጥቅስ ካመንክባት ህይወትህን የመለወጥ ኃይል አላት።
35
የሰዎች ህይወት ላይ ዕሴት ሳትጨምር ዕሴት አትጠብቅ።
አጋጣሚው ነው እንጂ አንተም ቢል ጌትስ ነህ። የእንግሊዝኛ ቋንቋን ቆማጣ ካልከው፥ አማርኛ ሙሉ ሽባ ሊሆን ነው።
ህይወት ትርጉም እስላልሰጠሃ ትርጉም አትሰጥህም። የብርሃኑን በር የሚከፍተው ቁልፍ የጨለማውንም ይበረግደዋል።
ፍልስፍና አይወለድም አይሞትም፤ ሁሌም አለ ሁሌም ይኖራል።
ለመብላት ምትኖር ነፍስ ምግብ ካጣች ትሞታለች፤ አላማዋ ምግብ ነው። ለመኖር ምትመገብ፥ ነገር ግን ከመኖር ባሻገር አላማ ያላት ነፍስ፥ ህያው ነች።
36
የመነፋፈቅ ተፈጥሯዊ ስሜት ምናልባት ካልሞተ፥ በፌስቡክ አለንጋ ክፉኛ ቆስሏል።
ባለህ ነገር መርካትን የመሰለ ሃብት የትም አታገኘውም።
መለወጥ የማትችለው ነገር ሲገጥምህ እራስህ ተለወጥ።
በጽሁፍ ማስቀመጥ የምፈልገውን ሃሳብ በህልሜ አየሁ። ወረቀትና እስክርቢቶ ስፈልግ ነቃሁ። ወረቀትና እስክርቢቶውን አገኘሁት። ሃሳቡ ግን ጠፍቷል።
እረዥም እድሜ መኖር ከፈለክ በቅድሚያ የህይወትን አጭርነት ተረዳ።
ልክ የሌለው ትዕግስት የዋህነትን፥ የዋህነት ቂልነትን ይወልዳል።
37
አትዘን ምክር ከሆነ አትደሰትም ምክር ነው። ሁለቱም መታፈን የለባቸውም።
ሳትታመም የሰወችን ህመም መረዳት አስቸጋሪ ነው። ከቃላት ጋር ተጣላሁ፥ ጦርነት ገጠምኩ፥ ተሸነፍኩ፥ በቃላት አበድኩ፥ ፍቅር ያዘኝ፥ ተጋባሁ ... አሁን እየተዋለድን ነው።
ቂምን የሚያህል ከባድ ሸክም ተሸክመህ መራመድ አስቸጋሪ ነው። በይቅርታ አራግፈህ ጣለው፥ ይቀልሃል።
የእውቀትህ አድማስ እየሰፋ ሲመጣ አንተ ለራስህ እያነስክ ትመጣለህ።
38
ስትደሰት አንዱ ቀን አንድ ሰዓት ይሆንብሃል። ስትሰቃይ አንዱ ሰዓት አንድ ቀን ይሆንብሃል። የስቃይ መጨረሻ የሞት አፈፍ (ጣር) ነው። ይሄኔ ታዲያ አንድ ሰከንድ ምን ያህል እንደሚረዝም መገመት ነው። ስለዚህ በላይኛው አገባህ ከሄድን ምናልባት ሞት ጊዜን አቁሞ ዘላለማዊ ያረገን ይሆን? ማን ያውቃል?
ህይወት በደስታ የተኳኳለች፥ ብዥታን የተላበሰች፥ በመከራ የታጀበች ሙሽራ ነች። ሙሽራው ደግሞ አንተ ነህ። ተስማምተህ ኑር!
ወይ በስነጽሁፍ ወይ በቲያትር ወይ በሙዚቃ ወይ በስእል ያልተማረከ ጭንቅላት ግቡን አልመታም።
ስግብግብነት ለካፒታሊዝም ነዳጅ፥ ለሶሻሊዝም ፍሬን፥ ለሶሻል-ዲሞክራት ፍሪሲዮን ነው።
ሸክሙ የተቃለለት ሰው፥ ሃብት ከተጨመረለት በላይ ሊያመሰግን ይገባዋል።
39
ስሜት ተዛማች ነው፥ አጠገብህ ላሉት ሰዎች ስትል እራስህን ተቆጣጠረው።
በራስ ከመሸነፍ በሰው መሸነፍ ይሻላል። እድሜን እንደ ብር ከባንክ መበደር ቢቻል ሞት ይወደዳል።
ትህትናን የተላበሰ ሰው ባዶ እራቁቱን ቢሆንም ያምርበታል።
በአመጣጥ ካየኽው ሌባ ከፖሊስ ቀደምት ነው፤ በጥበቡም እንደዛው።
ፍጹማዊ-ምንምነትን (መጥፋትን) ከሞት ጋር ሳዛምደው የድብርት ስሜት ይጫጫነኛል።
እራስህን አስገድደኽው ሳይሆን በእራስህ ስሜት ተነሳሽነት የምታደረገው ጉዞ፥ ብዙ እርቀት ይወስደሃል፥ መጨረሻውም ያማረ ነው።
40
ገነት ለመግባት መጀመሪያ ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ የገባት አንዲት እናት ከትንሽ ልጇ የተሰጣት ምክር፥ ቁርጥ ያለ “መጀመሪያ መሞት አለብሽ!” የሚል መልስ ነበር። እንደ ልጇ የዋህ ብትሆን ምናልባት ለመግባት ምንም ማድረግ ላይጠበቅባት ይችል ነበር።
እውነት ነው አንተ ከሌሎቹ የተለየህ ሰው ነህ! እንደ እኔ፥ እንደ እሱ፥ እንደ እሷ፥ እንደ ማንኛውም ሰው!
ውስብስብ የሆነን ሃሳብ በቀላል ቋንቋ መግለጽ ታላቅ ችሎታ ይጠይቃል።
ነጻነት ስሟ ነው ነጻ፤ ከባድ ዋጋ ታስከፍላለች!
41
ከዛሬ ሁለት ሺ አመት በፊትም “ወይ ዘንድሮ” ይባል ነበር። ድሮ ወይ ዘንድሮ፥ አሁን ወይ ዘንድሮ፥ ነገም ወይ ዘንድሮ፥ አቤት በል የታለህ የተሻልከው ኑሮ፥ ታለቅሳለች ህይወት ተማራ በሮሮ።
እንቅልፍና ሞት ወንድማማቾች ናቸው ሲሉ ሰማሁ፤ እኔ ግን አልተስማማሁም። የመጀመሪያው ሲወስድህ እያዝናና ነው፤ የሁለተኛው ግን እያሰቃየ።
አንድ ሚልየን ብር ጠረጴዛው ላይ ተቀምጧል። ብሩን ከአንተ ትይዩ ከተቀመጠ አንድ የማታውቀው ሰው ጋር መካፈል አለብህ። ስንቱን አስቀርተህ ስንቱን እንደምትሰጠው አንተ ትወስናለህ። ሰውየው ግን ገንዘቡን ካልተቀበለህ ሁለታችሁም ምንም አታገኙም። ያለህ አንድ እድል ብቻ ነው። መነጋገር አትችሉም። ለውሳኔው 20 ሰከንድ ተሰጥቶሃል።
42
ሰፈር ስደርስ ሰፈርተኛው ተሰብስቦ ያለቅሳል። ምንድን ነው ብዬ ግራ ገባኝ። ከለቀስተኛው ትንሽ አለፍ ብሎ የመብራት ሃይል መኪና ቆሟል። ተበላሽቶ የነበረው የሰፈራችን መብራት ከአንድ አመት ቡኋላ ሊሰራ ነው። እኔም አብሬ በደስታ አለቀስኩ።
ለራስህ ካላህ ግምት በላይ ልትሸጥ አትችልም። ተራ የሆነን ነገር ወደ ተራራ የመለወጥ ጥበብ ትትርና ይባላል።
ከእውቀት ስፋት ይልቅ ጥልቀት የተሻለ ውጤት ያመጣል፤ ስፋት አያልቅም አይጨበጥም። ጥለቅ፥ አንድ ነገር ላይ ብቻ አተኩር!
ብዙ ጊዜ ሰዎች ከምትመክራቸው ይልቅ ብትረዳቸው ይመርጣሉ።
ምክር የሚያበዛ ሰው ተግባር ላይ ደካማ ነው።
43
እራሱን ሳይወድ ሰውን የሚወድ ሰው ለጥቃት የተጋለጠ ነው። ሰውን ሳይወድ እራሱን የሚወድ ሰው ለትችት የተጋለጠ ነው። ራሱንም ሰውንም የማይወድ ሰው፥ ለዱር እንስሳ የተጋለጠ ነው።
ብዙ ግልጽ መሆንም እራቁትን ያስቀራል። ኃቀኛ ሰው አንድ ውሸት ከተናገረ ውሸታም ይባላል፤ ቀጣፊ ሰው አንድ እውነት ከተናገረ ጻድቅ ነው።
ስዕል መመልከት ከፊልም በላይ ይመስጠኛል፤ ከስዕሉ እይታ በስተጀርባ ያለውን ታሪክ በጭንቅላቴ እንደፈለኩ አቀናብረዋለሁ።
የህይወት ድብልቅልቅነት ከስኬት ጋር ሲዛመድ እድል ይባላል፤ የህይወት ድብልቅልቅነት ከውድቀት ጋር ሲዛመድ ግን እጣፈንታ?
ለአንዳንዱ፥ ጊዜ ወርቅ ነው፥ ለአንዳንዱ ደግሞ ትከሻ ላይ የተጫነ ከባድ ድንጋይ።
44
እያስተማርከው መሆኑን ሳያውቅ ካንተ የተማረ ሰው፥ ትምህርቱን መቼም አይረሳውም።
አሪፍ አስተማሪ አስተማሪነቱን አያሳውቅም። ጊዜን እንደ ሸቀጥ እርስ በእርስ ብንሻሻጥ፥ የማይረቡ ሰዎች ከዚህ ዓለም በፍጥነት ይጠፈሉ።
ውስጣዊ መነሳሳት የሌለው ሰው የሚንቀሳቀስ ሬሳ ነው።
ስለነገሮች መመራመር ያላቸው ፍላጎትና ጉጉት ልክ እንደ ህጻናት የሆኑ አዋቂወች ሳይንቲስቶች ይባላሉ።
ተራራውን ማንቀሳቀስ ከፈለክ ውስጥህ ያለውን መነሳሳት ቀስቅሰው።
ችግሩን በሶስት ከፍለህ ብታየው በቀላሉ ትፈታዋለህ፦ ወይ ከአንተ ነው፥ ወይ ከችግሩ ነው፥ ወይ ከመፍትሄው ነው፥ ወይም ከተጠቀሱት ሶስቱ ከሁለቱ። ሆኖም ግን ችግሩ ከሶስቱም ከሆነ፥ መፍትሄውን አግኝተህዋል።
45
ሃብታም መሆን መፈለግ፥ እሺ ሁላችንም ውስጥ ያለ ነገር ነው፥ ምክንያታዊም ነው። እኔ የማይገቡኝ ታዋቂ መሆን የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው!
አንድ ቀን ዘና ብዬ እየተራመድኩ ስሄድ ከአንበሳ ጋር ፊትለፊት ተገጣጠምን። አካባቢዬን ስቃኝ ማንም ሰው አጠገቤ አልነበረም። ከለስላሳ ጠርሙስና ከድንች ጥብስ በስተቀር በእጄ ምንም አልያዝኩም። የአካባቢው ጭር ማለት ውስጤን ፍርሃት ለቀቀበት። አይን ለአይን ተፋጠጥን። ወደኋላ ተንቀሳቀስኩ፥ ቀስ እያለ ወደ እኔ መምጣት ጀመረ። የአንበሳው ግቢ አጥር ጋር ሲደርስ ቆመ።
“ሰዎችና እንስሳት” የሚለውን ወደ “እንስሳት” ብናሳጥረውስ? ልዩነቱ ከቀን ወደ ቀን እየጠበበ መቷል!
የበሬ ስጋ፦ ለበሬው የእድሜ ልክ የትጋት ውጤት፥ ለድግስተኛ የአንድ ቀን ፌሽታና ሃሴት።
አእምሮዬ ሊከዳኝ አስቦ እራሱን ማሸነፍ አልቻለም። ባህላችን አደጋ ውስጥ ወድቋል! የባህል ሓኪም ጥሩ!
46
ንቃተ ህሊናህ እንዲፈንጥቅ ከፈለክ፥ የጨለማ እስርቤት ግባ። ጨለማው፥ ተፈጥሯዊ ብርሃንህን ያጎላዋል፤ ጠባቡ ክፍል፥ የዕይታ አድማስህን ያሰፋዋል። በፍጹም ማምለጥ እንደማትችል ማወቅህ፥ በእጅህ ያለውን ነገር እስከመጨረሻው እንድትጠቀመው ያደርግሃል።
ደስተኛ ሁን የሚሉኝ ቆይ፥ መርጬ ያዘንኩ መሰላቸው እንዴ!
ያለፈቃድህ ሰዎች በከፍተኛ ወለድ የሚሰጡህ ብድር፦ ስጦታ።
የፈለከውን ያህል ገንዘብ ይሰጠሃል ተባልክ እንበል። ምን ያህል ትፈልጋለህ? 5 ሰከንድ ብቻ ተሰቶሃል፥ ጥራው!
ስራው አስደሳች ከሆነ ታዲያ ለምን ደሞዝ ትከፍለኛለህ?
እሩብ እንጀራ የሚባል ነገር እንሰማ ይሆን? እንጀራም የአንባሻ እጣፈንታ እንዳይገጥመው ፈራሁ።
47
እንኳን ወደ ኢትዮጵያ በሰላም መጣቹህ! እባካችሁ ካሌንደራችሁን በ300 ዓመት ወደኋላ መልሱት።
በጥልቀት ሳስብ በሃሳብ እሰጥማለሁ፥ ግን በህይወት አለሁ፥ እተነፍሳለሁ። ሃሳብ ማለት ለእኔ ህይወት ማለት ነው!
ጥልቅ ስሜት ውስጥ ተኹኖ የተጻፈን ነገር፥ ጥልቅ ስሜት ውስጥ ካልሆንክ አትረዳውም።
ከራሳቸው ጋር ለማውራት ለራሳቸው ጊዜ የሚሰጡ ሰዎች ከሌሎች በተሻለ ምክንያታዊ ናቸው።
በፊት በራሴ ላይ እጮህ ነበር፤ ሚዛነዊ አይደለም፥ ተውኩት። ቀስ ብዬ በነገሮች መጮህ ጀመርኩ፤ ሚዛናዊ አይደለም፥ ተውኩት። አሁን በማንም ላይ አልጮህም፤ ሚዛኑን ከራሴ ላይ አንስቸዋለሁ።
48
ስለ ሎጂክ (Logic) ልጽፍ ብዬ፥ ዲክሽነሪ ላይ የአማርኛ ትርጉሙ “ስነአመክንድ” መሆኑን ተማርኩ። “ስነአመክንድ” ብዬ ብጽፍ ማንም አይረዳኝም ብዬ ስላሰብኩ ተውኩት።
አብዛኛው ሰው ዝምተኛውን ጆሮ እንጂ ለፍላፊውን ምላስህን እንድትሰጠው አይፈልግም። ዝም ብለህ አድምጠው። ተወጥሯል፥ አስተንፍሰው፥ የአንተ ጆሮ፥ እፎይታው ነው።
ጩሉሌ ሰዎች በጣም ስለሚጮሁ ለማደን ቀላል ናቸው።
እንዳልረሳ እያሰብኩ፥ እሱንም እረሳሁት። ከመሃይምና ሆዳም ሰዎች ጋር ሳወራ የበታችነት ስሜት ይሰማኛል።
ለሰዎች ያለህ ከበሬታ እራስህን እስከማዋረድ ጥግ መድረስ የለበትም።
49
የመንግስት ቁጥጥር ባይኖር፥ የሰው ግብረገባዊነት ፈተና ውስጥ ይወድቃል።
በወዳጅነት መንፈስ የተነገረህን ነገር በጥላቻ መንፈስ ውስጥ ካለህ አይገባህም።
ፈላስፎች የብዙ ሰው ጫማ ተጫምተው መጓዝ ያስደስታቸዋል። የህይወት ተሞክሯቸው የገዘፈ ነው። አንድ አካል ቢኖራቸውም መንፈሳቸው ግን ብዙ ነው።
በሌንስ መነጽር የተሰበሰበ የጸሃይ ብርሃን ወረቀት ያነዳል። የተሰበሰበ አዕምሮ ዓለም ይለውጣል። የለውጥ ሀ-ሁ ከዚህ ይጀምራል።
አለማችን ላይ ያለው የሰው ልጅ ባህሪ ተመሳሳይ ነው፤ እዚህ ምትወደድ ከሆንክ እዛም ትወደዳለህ፥ እዚህ ምትጠላ ከሆንክ እዛም ትጠላለህ።
50
ጭራቁም ውስጥህ አለ፥ ጻድቁም ውስጥህ አለ። ጥያቄው፥ ይበልጥ ገመዱን ሚጎትተው የትኛው ነው?
የራስህን ባህሪ መላበስ ያኮራል። እራስህን መቀበል፥ መሆን እንጂ አለማስመሰል፥ ከራስ ጋር ተስማምቶ መኖር። የደስታ መሰረት/ምንጭ ከዚህ አያልፍም።
አንተን ለማበሳጨት የመጣን ሰው፥ ካልተበሳጨህለት ተበሳጭቶ ይመለሳል፥ ከሳቅበት ተጣልቶህ ይሄዳል፥ ከተረዳኽው ግን አሰተማሪው ያደርግሃል።
ሁሉን ሰው ማስደሰት የሚፈልግ ሰው፥ የገና አባት ነው።
እድሜ ልክህን መሮጥ ካልፈለክ በስተቀር፥ አትሽሽ። ጉልበትህን ቆጥብ። ነገሮችን ተጋፈጥ!
51
ጥፈትህን አምነህ ስትቀበል፥ ለሰወች የምታስተላልፈው መልዕክት አለ፦ እኔ ፍጹም አይደለሁም እያልካቸው ነው። እኔ ደካማ ነኝ እያልካቸው ነው። እኔ ልታረም፥ ልማር ፈቃደኛ ነኝ እያልካቸው ነው። ይህ ደግሞ ሁላችንም አንድ የሚያደረገን፥ ፍጹም ሰዋዊ የሆነ መገለጫችን ነው። ልናፍርበት አይገባም። ጥፈቱን ሳያድበሰብስ አምኖ የሚቀበልን ሰው፥ ሁላችንም እንቀበለዋለን፥ እናከብረዋለን።
የሚያሳዝነው፥ የአንድ እስትንፈስን ዋጋ የምንረዳው የመጨረሻ ሰአታችን ላይ መሆኑ ነው።
ሁልጊዜም ስጦታ የሆነች፥ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ የማናስተውላት ነገር “የአሁኗን ሰዓት” ነው።
ቆሜ ከምደማ እሮጬ ብሞት ይሻለኛል።
52
የሰው ልጅ ላለፉት 3,400 ዓመታት መሬት ላይ ሲኖር፥ 92 በመቶ ጊዜውን በጦርነት አሳልፏል። ጦርነት ስግብግብነት የወለደው ዲቃላ ነው፤ ሁሌም ከታሪክ ለማይማረው ለጦረኛው የሰው ልጅ ግን፥ የማይጠረቃ ሆዱን ማሳበጫ መሳሪያ ነው።
ልጅ ሆነን እንደዛ ስንቦርቅ፥ በእውነት ደስታው ገብቶን ነው? እናስታውሰዋለን?
አንዳንዴ በህይወትህ ውስጥ፥ አንተ ባታምንባቸውም እነሱ የሚያምኑብህ ሰዎች ያጋጥሙሃል። እነሱን ነው ማመን!
የብዙ አማራጭ መኖር ለእርካታ ዋስትና አይሆንም። እንደውም ለብስጭትና ለቅሬታ ዋስትና ነው።
በእጣፈንታ ባላምንም ከባህሪያችን ጋር የተቆራኘ ዝምድና እንዳለው ግን ይሰማኛል።
53
እነዛን ሱፍ ለባሾች፥ እነዛን እኛ ብቻ ነን አዋቂ፥ እኛ ብቻ እንሰማ የሚሉትን፥ ጎርነን ያለ ድምጽ ያላቸው መሪዎች፦ ድምጻቸውን በቆንጅዬ የሴት ልጅ ድምጽ መለወጥ ብችል፥ አረገው ነበር።
የሰው ልጅ ወዶ አይቸገርም፥ ወዶ አይራብም፥ አይጠማም። ሳይወዱ ያለምርጫቸው ችግርን ለሚጋፈጡ መሰሎችህ እጅህን ዘርጋ።
ሰው በችግር ጊዜ ልቡን፥ በጥጋብ ጊዜ ስሜቱን ያዳምጣል።
ማየት ማመን ነው ይባላል። አይነስውራን ለማመን ብቁ አይደሉም ማለት ነው?
ሁልጊዜ፥ “አሁን የማደርገውን ነገር ለምንድን ነው የማደርገው?” ብለህ እራስህን ጠይቅ። አጥጋቢ መልስ ካላገኘህ መስመርህን አስተካክል።
የወንድ ልጅ ስሜት ትኩስና ቶሎ ሚገነፍል ነው፤ የሴት ልጅ ስሜት የረጋና የተረጋጋ ነው።
54
ሴት ልጅ በክብ ትመሰላለች፤ አቃፊ፥ ከልካይ፥ አራሚ፥ ኮትኳች፥ መካሪ፥ ተራማጅ፥ ሁሉን አቀፍ።
መንጻትን ፈለኩ፥ ግን ደግሞ የቆሸሽኩ አልመሰለኝም።
ጨርቁን የጣለ ሰው የተፈጥሮ ትክክለኛ ነጸብራቅ ነው። የመጀመሪያውን አዳም የመምሰል ፍላጎት ምንም ስህተት የለውም።
አንተ እራስህ ለራስህ ከከበድከው ለማን ልትቀለው ነው?
ቀደምት ለመሆን፥ የተቀደምክባቸውን ነገሮች በጠቅላላ ማወቅ ግድ ይለሃል።
አላማ የሌላት ህይወት አላማ ካላት ህይወት ይበልጥ እንግልት ይጠብቃታል።
55
ሁሉም ነገር ተለዋዋጭ መሆኑን አምነህ ተቀበል፤ ደግና የዋህ የምትላቸው ሰወችም ቢሆኑ የራሳቸው ጊዜ አላቸው።
ሳታስበው የምትሰራው ስራ፥ አስበኽው ከምትሰራው የበለጠ ውጤታማ ያደርግሃል።
እንደኔ እንደኔ፥ 95 በመቶው የህይወት ሂደት ለእድል የተተወ ነው። ይህን እውነታ ተቀብሎ ህይወትን መምራት ታላቅነት ነው።
የሚያስፈልግህ እንደ አልማዝ የጠነከረ እምነትና እንደ ጥጥ የሳሳ ልብ ነው።
ሁሉንም ሰው ለማስደሰት መሞከር ቂልነት ነው፥ ሁሉንም ሰው ለመረዳት መሞከር ታላቅነት ነው።
ወላዋይ ሰው በራስ መተማመኑ ደካማ ነው። ጥሩ እንቅልፍ ጥሩ ሜዲቴሽን ነው።
56
ለጥቃቅን ነገሮች ቦታ የምትሰጥ ሰው ከሆንክ፥ ትላልቅ ነገሮችን እያደረክ አይደለምና እንደገና እራስህን ፈትሽ።
ብትወደድ ወይስ ብትፈራ? የቱን ትመርጣለህ? መጻሃፍትን የሚያነብ ሰው በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንኳን ያንጸባርቃል።
ሶስት አይነት ሰዎች ይታዩኛል፦ እድለኛ፥ እድለቢስ፥ ቀናተኛ።
መልካሙንም መጥፎውንም በእኩል መጠን ተቆጣጠራቸው። መልካም ሲገጥምህ ብዙ አትፈንጥዝ፥ መጥፎ ሲገጥምህ ብዙ አትደናገር።
ስሜታዊ ስትሆን ምላስህን ሰብስብ፥ ምክንያታዊ ስትሆን ምላስህን ዘርጋ።
አሪፍ እንግዳ፥ መቼ ተሰናብቶ መውጣት እንዳለበት ስዓቱን ያውቃል።
57
ገንዘብ የህይወት ጥቁር የዓይን መነጽር ነው፤ ህይወትን በከለር እንዳንመለከት ትልቅ እንቅፈት!
አሁን ባለህበት ማንነት፥ የኢኮኖሚም ሆነ የማህበረሰብ ደረጃህ ሳይለወጥ ለዘላለም መኖር ትፈልጋለህ?
ሚስትህ እንደድንገት የዓለም ጠበብቶች ተራቀው የሰሯት እሮቦት ሆና ተገኘች። አሁንም ታፈቅራታለህ?
የነበረና የሚኖር (የአልፈና ኦሜጋ) ሃሳብ ለህያዋን አይመጥንም።
ትኩረትና ጉጉት ካለህ ውጤታማ ነህ፤ ስነስርዓትና ጽናትን ከጨመርክበት ስኬታማ ትሆናለህ።
ስለነገሮች በደንብ ማወቅ ከፈለክ፥ አስተምር። የምታየውን ነገር ማመን ካቃተህ፥ የማታየውን ነገር እንዴት ማመን ትችላለህ?
58
ስለምታየው ነገር ሁላ ለማወቅ የምትጓጓ ከሆንክ አርቲስት ነክ ነህ። ሰለ አንድ ስላስተዋልከው ነገር የጠለቀ እውቀት እንዲኖርህ የምትጓጓ ከሆንክ ሳይንቲስት ነክ ነህ።
ሞት ምንም ጣር ባይኖረው፥ ወይም እንደ ፌስቡክ በቀላሉ ሳይንአውት (Signout) እያልን መቀላቀል ብንችል፥ የዓለም የህዝብ ብዛት በአንድ ሌሊት በግማሽ ሚቀንስ ይመስለኛል።
አትግደል ሲባል፥ ነፍሳትንም ያጠቃል ይሆን? ለእኔ ደስታ ማለት፥ እኔ እራሴን ሆኜ ሳገኘው የሚሰጠኝ ስሜት ነው።
ልታይ ልታይ ባይነት መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁላችንም ውስጥ አለ።
ፈልገህ ማግኘት ከቻልክ፥ አግኝተህ ማሳየትን እንዳትረሳ።
59
እራስህን እንድትሆን የሚፈቅድልህ ሰው፥ አስተዋይና ጠቢብ ነው።
ከተጠራጣሪ ሰው፥ የዋህና ሁሉን አማኝ ሰው፥ ለሰው የቀረበ ነው።
ኢንተርኔት የሰዎችን ተፈጥሯዊ ስሜት ሰለቃቅቶ በልቶታል።
የቴክኖሎጂ ዘመን ደስታ፥ ጥርሱ “በብር” (በገንዘብ) (በብልጭልጭ ነገር) የተለበጠ ነው።
ጥሮ ግሮ መብላት እንጂ ምቾት ለደስታ ዋስትና አይደለም።
ናፍቆት የነገሮች እውነተኛ ዋጋ መመዘኛ መሳሪያ ነው።
የእድሜ እርዝመት በትዝታ እንጂ በትንቢት አይለካም።
60
ህይወት ትርጉም እንዲኖራት አላማና ግብ ያስፈልጋታል።
እራስህን ስታመጥቀው ብቻ ሳይሆን ስታዘግመውም ጥሩ ስሜት ሊሰማህ ይችላል።
መጥቆ የሄደን ሰው ጊዜ ትጠብቀዋለች። ሸክም ከመሆን ተሸካሚ መሆን ተመራጭ ነው። ስለራስህ እራስህ እንጂ ሌላ ሰው እንዲነግርህ በፍጹም አትፍቀድ።
በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብትሆን፥ ወሰን ይኑርህ። ተጠራጣሪ ሰው ጥርጣሬው ይገድለዋል፤ የዋህን ሰው እምነት ይገድለዋል።
እያንዳንዳችን ውስጥ ያለውን ጭራቅ ወይ ርሃብ ወይ ስግብግብነት ያወጣዋል።
61
ሁላችንም ማንነታችን ጠፍቶብናል፤ አፋልጉኝ እንለጥፍ!
መረሳትን ሚፈልጉ ነገር ግን ሁሌም ሚናፈቁ ሰዎች ቢሞቱ እንኳን መአዛቸው ለዘለዓለም ያውዳል።
ለሰዎች በጎ ከማድረግ በስተጀርባ ሁሌም ጥቅማጥቅማዊ ምክንያት አለ።
የተወለድኩበት ቀን የሚከበርልኝ ቀኑን ማን አውቆት ኖሯል? የምሞትበትን ቀን የሚያውቀው እስኪ እሱ ማን ነው?
መሰልጠን ማለት እውነተኛ ማንነታችንን በፍጹም መካድ ማለት ነው።
ሃይለኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ሚያመነጩ ሰዎች አትንኩኝ ባዮች ናቸው።
ከምወደድ ይልቅ መፈራትን እመርጣለሁ፥ ከምደፈር ይልቅ መጠላትን እመርጣለሁ።
62
እንዳልነበርኩ ማውቀው ከነበርኩ ቡኋላ ነው። አለሁ ይባላል?
በቆርቆሮ ራስ የሚስተዳደር ሕዝብ፥ ትንሽ ሲነካ እንደ ባዶ ቆርቆሮ በጣም ይጮሃል።
ሌባ መሪ ሌባ ሕዝብን ይወልዳል። ሕዝቡ ሌባ ከሆነ፥ መጀመሪያ መሪው ሌባ ነበር ማለት ነው።
ሁሉም ሰው የልቡን ቢያወራ፥ ልባዊ እውነተኛነት አጠራጣሪ ይሆን ነበር።
ሁሌም ልንፍርድባት የሚዳዳን ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ልንቀበላት የሚገባን ነገር እድል ነች።
ሁልጊዜ መድፈን ያቃተኝ ክፍት ነገር ያለ ይመስለኛል። ሙሉ ሰው እንደማልሆን አምኜ ተቀብያለሁ።
የደስታ ጅማሮ፥ እራስን ሙሉ በሙሉ አውቆ መቀበል መቻል ነው።
63
እውቀት ሳይሆን፥ ሰወችን የመረዳት ችሎታ፥ ህይወትህን የበለጠ ጣፋጭ ያደርገዋል።
ሰው በመሆንህ ብቻ እድለኛ ነህ፤ ለሰዎች መኖር ከቻልክ ደግሞ በጣም እድለኛ ነህ።
መንፈሳዊነት ለህይወት ትርምስ ዓይነተኛ እንክብል ነው። እንደ ትርምሱ ጥንካሬ ሃይማኖትም የመጨረሻ መድሃኒት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ወዳጅ የሌለው ሰው የተቃጠለ አምፖል ነው፤ አይበራም፥ አያበራም።
ወይ ነው ወይ አይደለም፤ ወይ ነህ ወይ አይደለህም፤ ከዚህ የተረፈው ትንቢት እና መላምት ነው።
የህይወት ሚስጥር በእጅህ እንዳለ ከተሰማቸው፥ ታማኝ ተከታዮችህ ልታደርጋቸው ትችላለህ።
ተገቢ ያልሆነ አድናቆት ገዳይ ነው።
64
መግለጽና ማብራራት የምትችለው ጭንቀት እንደጭንቀት አይቆጠርም።
የሰዎች አለማወቅ የሚያስፈነጥዘው ሰው ከፍየል ወጠጤ ጋር ይዛመዳል።
የራስህን ሸክም ለማቃለል መንፈሳዊ ሁን፥ የሰዎችን ሸክም ለማቃለል ሃይማኖተኛ ሁን።
በምትደሰተው መጠን ልትከፈ እንደምትችል አስብ። ያልተገደበ ነጻነት ሁልጊዜም በህግና በደንብ መገደቡ አይቀርም።
ያልተገደበ ነጻነት ስርዓት አልበኝነትን ያስከትላል። የተገደበ ነጻነት አንባገነንነትን ያስከትላል።
የፈለኩትን የማድረግ ነጻነት አለኝ፤ የፈለኩትን የማግኝት ነጻነት ግን የለኝም።
ተጽእኖ የማይፈጥርብህ ገደብ፥ ነጻነትህን እንደነፈገህ ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም።
65
ለሰው ልጅ ብቸኛው ስጋት የሰው ልጅ እራሱ ነው። እንዳትሞት ከፈለክ ለዓላማህ ሙት። አስተማሪ ያልሆነ ፍርድ እንደፍርድ አይቆጠርም። የሞት ቀጠሮ መዘግየት፥ እራስን ማጥፋት ሊያስከትል ይችላል።
ፈጣሪያችን አንድ ቢሆንም አምላካችን ሊለያይ ይችላል።
አምላክህ በሰው ተመስሎ ወደ መሬት ቢወርድ አምላክነቱን እንዴት ታረጋግጣለህ?
ስለምትፈልገው ነገር ግልጽ ስትሆን፥ የምትፈልገው ነገር ይገለጽለሃል።
66
እኔ ነኝ ከህሊናዬ ጋር የማወራው? ህሊናዬ ነው ከእኔ ጋር የሚያወራው? አንድ ከሆንን እሺ ለምን እንደ ሁለት እናወራለን? ሁሌም ግራ የሚገባ ጥያቄ!
የጥርጣሬህ መጠን እንደ እውቀትህ ልኬት ይለያያል።
ዘረኝነት፥ መሃይምነት የፈጠረው የፖለቲካ ማዕበል ነው።
ብልጠት ለፖለቲከኞች፤ ብልሃት ለመሪዎች፤ ብስለት ለተማሪዎች ነው።
ጭንቅላትህን ጊዜው ሳያልፍ ተጠቀምበት። የኢንተርኔቱ እንቆቅልሽ፦ መረጃው እንደ ጉድ ይጎርፋል፥ መምረጥ ግን ተስኖናል፥ መረዳትም አቅቶናል።
67
የፌስቡክ ማንነትህን ከእውነተኛ ማንነትህ አስበልጠህ ከወደድከው፥ የፌስቡክ አሻንጉሊት ሆነሃል ማለት ነው።
ብችል መሞከር የምፈልገው ነገር ሞትን ቀምሶ መመለስ ነበር።
ጠመንጃ ሰዎችን ይጠብቃል ወይስ ያጠፋል? ፍሬን የበጠሰ አንድ ባቡር ወደ አንተ አቅጣጫ እየገሰገሰ ነው። ፊትለፊት ያሉት 10 የቀን ሰራተኞች የባቡሩን አደጋ ማምለጥ በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ተገንዝበሃል። የባቡሩን አቅጣጫ ማስለወጫ መሳሪያ ከጎንህ አለ። ባቡሩን አቅጣጫ ብታስለውጠው፥ በሌላኛው ሓዲድ ላይ ያሉት 2 የቀን ሰራተኞች ብቻ ስለሆኑ፥ የሞት ቁጥሩን በ 8 ትቀንሰዋለህ። ባቡሩን አቅጣጫ ታስለውጠዋለህ? ለምን?
68
ከላይ በተጠቀሰው ክስተት መሰረት፥ ከሁለቱ አንዱዋ የቀን ሰራተኛ እናትህ ብትሆን ውሳኔህን ትለውጠዋለህ? ለምን?
ዘረኝነት የሚወገደው የሰው ልጅ ከኤልያኖች ጋር ጦርነት የገጠመ ዕለት ነው።
የታክሲውን ሰልፍ ያየ፥ በቀበሌው አይቀልድም። አንጻራዊነት እንጂ ፍጹማዊነት የሚባል ነገር የለም። አለማችን ሚሊየን ጊዜ ጠፍታ ሚሊየን ጊዜ ብትፈጠር፥ ሚሊየን ጊዜ ተቀዳሚ ሆኖ የሚፈጠረው የእውቀት ዘርፍ ፍልስፍና ነው።
ከራስህ ጋር ስታወራ ጥንቃቄ አድርግ፥ ገንቢ እንጂ አፍራሽ ነገሮችን ከውስጥህ አውጣ። ሰው ከሚያስበው ነገር ውጭ ሊሆን አይችልም።
ስዎች ስለአንተ ያላቸው አስተያየት፥ አንተ ስለራስህ ካለህ አስተያየት ጋር ተመሳሳይ ነው።
69
አስመስላለሁ ብለህ መስለህ እንዳትጠፈ፤ የራስህን ማንነት ከምንም በላይ ጠብቀው።
ትምህርትን ከመምህራን፥ እውቀትን ከራስህ ትቀስማለህ።
ሀ ብለህ ከጀመርክ ፐ ብለህ ለመጨረስ ግማሽ መንገድ ተጉዘሃል።
እራሳቸውን ተጠያቂ የሚያደርጉ ሰዎች የጀግናና የስኬታማ ሰዎች ተምሳሌቶች ናቸው።
በመፈለግ ያጠፋሁትን ጊዜ ሳገኝው ወዲያውኑ ተካስኩ።
ለብዙ ነገሮች ጉጉ መሆኔ ሽባ አድርጎኛል። በፈለከው መጠን አንተም ትፈለጋለህ። በደንብ ለመፈተን መጀመሪያ በደንብ ተፈተን።
70
የትህትና ደጋፊ ነኝ፥ የዋህ ግን አይደለሁም። ከአንተ ጋር በኃቀኝነት እስከመጨረሻው ሊዘልቅ የሚችለው ብቸኛ ነገር “እውቀትህ” ነው።
ልትገነፍል ስታስብ፥ ከዛሬ 100 ዓመት ቡኃላ እራስህን ሳለው፥ ትሰክናለህ።
ስለራሴ ያለኝን ግምት ካሳነስክብኝ፥ ስለራስህ ያለህን ግምት እገለዋለሁ።
እነዛ ቁጫጮች፥ ሰዎችን በትንሽ በትልቁ የሚገምቱ፥ ለምን ከግዙፎቹ የአለማችን አዋቂ ከበርቴዎች እንደማይማሩ አይገባኝም።
ሌባ መሆን ብርቅ አይደለም፥ እንደውም ተራ ነገር ነው። በፍጹም እንደስልጣኔ ሊታይ ግን አይገባም!
ተረት ተረት ስትለው የላም በረት ከሚልህ ሰው ጋር ቁም ነገር ማውራት አትችልም።
ሰዎችን ተጠራጠር፥ እራስህን በፍጹም እመን።
71
በቃኝን የሚያቅ ሁሌም ትርፈማ ነው። የሰው ልጅ ከነቃ፥ አይሰራም ጥበቃ። ጀግና ሰው የመሰለውን ይሆናል፥ ጀዝባ ሰው ያስመሰልከውን ይሆናል።
ካፒታሊዝም እራሱን ጠልፎ ይጥላል፥ ሶሻሊዝም በሰው ተጠልፎ ይወድቃል።
ስርዓት አልበኝነት እና አብዮት፥ የኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ደመና ይዞት የመጣ ዝናብ ነው።
ዲሞክራቲክ መንግስት በ51% የህዝብ ምርጫ 49% ተቃዋሚ ይዞ ያሸንፋል፤ አምባገነን መንግስት በ99% የህዝብ ምርጫ፥ ምን ያህል ተቃዋሚ እንዳለው ሳይታወቅ ያሸንፋል።
እጅና እግርህን በካቴና አስሮ፥ ሰርተህ ብላ፥ ከእኔ አትጠብቅ ከሚል መንግስት ይሰውር።
72
ሶሻሊዝም ለሕዝቦች ካፒታሊዝም ለሃብታሞች ይመቻል። ሶሻሊዝም ብዙ ድሆችን ካፒታሊዝም ብዙ ሆዳሞችን ይፈለፍላል። ሁለቱም አይሰሩም። ቢሰራ ግን ሶሻሊዝም ተመራጭ ነበር።
መጀመሪያ በሕዝቦች አንድነት፣ መተማመንና የወደፊት እራዕይ ላይ ሳይሰራ ዝም ተብሎ ሰለ ብልጽግና መለፍለፍ ትርጉም አልባ ነው።
የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪወች ጊዜያቸውን አላግባብ እያጠፉ ይመስለኛል። ሰዉ ሁላ ፖለቲከኛ ሆኗል!
ካፒታሊዝም፥ ሶሻሊዝም፥ ማርክሲዝም፥ ሌኒኒዝም፥ ሊብራዝም፥ ኮንሰርቫቲዝም፥ አይዲያሊዝም፥ ማቴሪያሊዝም ዝም ዝም ዝም ... ይቀጥላል። ሁሉንም ዝሞች አንድ ዝም፥ ዝም ያሰኛቸዋል፤ ... ሂዩማኒዝም!
73
ሁላችንም የሎተሪ ውቅያኖስ ውስጥ ምንዋኝ ይመስለኛል። በጣም ጥቂት ሰዎች የሎተሪው እጣ ቶሎ ይደርሳቸዋል። አብዛኞች ሳይደርሳቸው ያልፋል፥ እነሱም እስከወዲያኛው ያልፋሉ።
ፈጣሪ ለመሆን ሞክር፥ አለዚያ ፈጣሪህን አክብር፥ ካልሆነ ግን ዝም በል!
ስለሌለው(ስለማይታየው) ነገር የምናምነው፥ ሲጀመር ስላለው(ስለሚታየው) ነገር ምን ያህል አምነንበት ነው?
አገልግሎቱን በብቸኝነት እየሰጠህ፥ ተገልጋዮችን “ውድ ደንበኛችን” እያሉ ማቆላመጥ ከስድብ አይተናነስም!
ጥሩ መሃይም ጥሩ ባሪያ ይወጣዋል። መነዳት ካልፈለክ መሪውን ጨብጠው።
74
ሓሳብህን አድንቀው፥ አክብረው፥ ውደደው፤ ወልዶኃልና!
ለተራ ሰው ሃሳብህን በግልጽ ማብራራት ካልቻልክ፥ ሲጀመር ሃሳቡን በደንብ አልተረዳኽውም ማለት ነው።
ለሓሳበ-ሰፊ ዓለም ጠባብ ነች። ከልብ ያልተደረገ ነገር እንዳልተደረገ ይቆጠራል። ቢል ጌትስ የወርቅ ቅብ መኪና ቢነዳ ማን ያምነዋል? በሜካፕ አይተሃት ካገባሃት፥ በትዳር ውስጥ ስትኖር ተጨማሪ ወጪ እንደሚጠብቅህ አስብ።
በመምስል እንጂ በማስመሰል ከፈጣሪህ ስጦታ መጠበቅ፥ ጅልነት ወይም/እና ከባድ ድፍረት ነው።
75
አሜሪካን ሀገር ደርሼ መጣሁ፥ አሁን ዩሮፕ ነኝ፥ አሁን ቻይና ገባሁ። የሃሳብ ነጻነት ቪዛ አይጠይቅም።
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ኑሮ አይደለም ለብር ለዶላር አይመችም።
እኩል ተፈጥረሃል፥ እኩል ትሞታለህ፥ እኩል ግን አትኖርም።
ከራሳችን ጋር ስንጣላ፥ ሁሌም ገንዘብ አስታራቂ ነው።
አፈታሪክ ከታሪክ ይሻላል፥ ወሬ እንጂ ስግብግብነት አሎለደውም።
ከአንበሳ ጋር ከመሯሯጥ ልክ እንደ ትንሿ ወፍ ከመሬት አራት ወይም አምስት ሜትር ከፍ የማለት ችሎታ ቢኖርህ የተሻለ ነው።
76
እርሃብ የጭንቅላት ሞተር ቁልፍ ነው፤ ጥጋብ የሃሳብ ፍሬን ነው።
ኃሳብህን እንደ ፍትፍት ፈትፍተህ ማጉረስ ካልቻልክ፥ ሲጀመር በደንብ አላላመጥከውም ማለት ነው።
ለማስመሰል የምታወጣውን ሃይል ለመሆን ብታወጣው በቀላሉ ስኬታማ ትሆን ነበር።
አስመሳይ ሰው አይመቸኝም፤ የእሱን እውነተኛ ማንነት ለማወቅ ጊዜ ማባከን አልፈልግም።
መሰረተቢስ ጭንቀት፥ መሰረቱ ከታወቀ ጭንቀት ይበልጥ አሳሳቢ ነው።
ቆርቆሮውን ባልመታውስ! ከቆርቆሮ ራስ ጋር ምን አደናቆረኝ።
አክብሮትና ትህትናን የተላበሰ ስብዕና ዘናጭ ነው።
77
አዕምሮህ ሆድህን ለማስደሰት ሳይሆን፥ ሆድህ አዕምሮህን ለማስደሰት መኖር አለበት።
ጥያቄ መጠየቅ ያቆምክለት ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቆርቆሮ ትሆናለህ።
የሚስጥራዊው ህይወት ትርጉም እንደፈቺው ይለያያል።
በስሜት የሚገለጽ ነገር በአንጻራዊነት ሚዛን ሊለካ አይችልም።
የሰከነ ጭንቅላት ማእበል ይፈጥራል፤ ቀዥቃዣ ጭንቅላት ሁከትን ይፈጥራል።
እርስ በእርስ መተማመን ሲሸረሸር ጸረ-አንድነት ያብባል።
ህይወት ልትሸከምህ እንጂ ሸክም ልትሆንብህ አይገባም።
78
ነገሮችን ስታፈቅራቸው ሚስጥራቸውን ይገልጹልሃል።
ተጠራጣሪ መሆን ለምርምር እንጂ ለወዳጅነት አይመችም።
ክፍት የሆነ ጭንቅላት ለማስገባት ብቻ ሳይሆን ለማሶጣትም አይቸገርም።
የውስጡ ሳይታይ የውጩን እዩኝ እዩኝ ባይነት ምን አመጣው?
ኃሳብ ቋንቋን እንጂ ቋንቋ ኃሳብን አሎለደውም! እንደ ፖሊስ ማሰብ የሚችል ሌባ አደገኛ ሌባ ነው፤ እንደ ሌባ ማሰብ የሚችል ፖሊስ አደገኛ ፖሊስ ነው።
አይን ሲጠፋ ልብ ይበራል።
79
በይበልጥ ግድ ሚሰጥህ አንድ ነገር ካለ፥ ግድየለሽ ሰው ትሆናለህ።
የወጣህ ከሆንክ የገባህ ነገር አለ ማለት ነው። የአልበርት አንስታይንን ሃሳብ ለማስረዳት አልበርት አንስታይንን መሆን አይጠበቅብህም።
እየበሰልክ ስትመጣ ብቸኝነት እየጣፈጠህ ይመጣል።
ደካማ ሰዎች በጥርጣሬ ይሞታሉ፥ ተራ ሰዎች እራሳቸውን ሳያውቁ ይሞታሉ፥ ጠበብት በናፍቆት ይሞታሉ።
ፍጹማዊነትን ፍለጋ እራስን በማጥፈት ይቋጫል። ዓለም ፍትሓዊ ብትሆን ፍልስፍና ባልተፈጠር ነበር። ሁሉም ነገር አሮጌና አላፊ ነው። በጊዜው አዲስነቱን ሳታደንቅ ግን አትለፍ!
80
አናሳዎቹ ልሂቃን፥ ለብዙኃኑ የተራሰው ትችት እራሳቸውን ማዘጋጀት አይጠበቅባቸውም።
በመንግስት የተመረጠ መንግስት እንጂ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ለሌብነት አያመችም።
ሲስተሙ ሲዘምን ቢርዮክራቶች ያኮርፈሉ። አንድ ቀን፥ “አሜሪካን የምትባል ሃያል ሀገር ነበረች” የምንልበት ቀን ይመጣል።
የመንግስት አልባ ሀገር ዜጋ፦ ሁሉም እኩል ተጠቃሚ፥ እኩል ተጎጂ ነው። በመንግስት የሚስተዳደር ሀገር ዜጋ፦ ጥቂቱ ተጠቃሚ ነው ብዙሃኑ ተጎጂ ነው።
ተስማምተን እንድንኖር በስርዓት ያስተዳድረናል ብለን የመረጥነው መንግስት፥ እኛን እርስ በእርስ እያባላ እራሱን ግን በስርዓት እያስተዳደረ ነው።
81
የብሔር ብሔረሰቦች አንድነት በተረጋረጠበት ሀገር ውስጥ፥ መታወቂያ ለማውጣት ብሔርን መጠየቅ ምን ማለት ነው?
የሰው ልጅ ከእንስሳት ብቻ ሳይሆን ከእጽዋትም መማር አለበት።
የዜጎች የውስጥ ሰላም ካልተረጋገጠ፥ የሀገር ሰላም ሊረጋገጥ አይችልም።
የሰውን ልጅ ለመረዳት፥ እራስን መረዳት ብቻ በቂ ነው።
መረጃ ወደ እውቀት የሚቀየረው ከተረዳኸው ነው። ድንቁርና እንጂ እውቀት ጥግ ሊኖረው አይገባም። እድለኛ ሰው ከሚቀበለው ይልቅ የሚሰጠው ያመዝናል።
እውቅና እውቀትህን ይዘርፍሃል።
82
በእድል የማያምን ሰው ለብስጭት የተጋለጠ ነው። ዋጋ ከሌለህ፥ ዋጋ የለህም! ዋጋ ካለህ፥ እራስህን ሸጠህ አትርፍበት።
የጭንቀት ምንጩ፥ መስጠት እንደምንችለው መጠን አለመስጠት ወይም መቀበል እንደምንችለው መጠን አለመቀበል መቻል ነው።
ለማፍቀር ያልተፈጠረ ልብ መፈቀር አይችልም። የምላስ ጥንካሬ ሰይፍ እስከሌለ ነው፥ የሰይፍ ጥንካሬ ብዕር እስከሌለ ነው።
ጥቂት ሰዎች ይናገራሉ፥ አብዛኛው ሰው ያወራል፥ ሁሉም ፖለቲሺያኖች ይለፈልፋሉ።
ስለባህሪህ እንጂ ስለ ገጸባህሪህ አታስብ። ባህሪ፥ አንተ ስለራስህ ያለህ እይታ ነው። ገጸባህሪ፥ ሰዎች ስለአንተ ያላቸው ገጽታ ነው።
83
የቁምነገረ ሚስጥር ገብቶሃል፥ ግን አንተ ውስጥ አላገኝኽውም፤ እሱ ደግሞ መልሶ ያስጨንቅሃል።
የፍቅር ኃይል አልማዝ ይሰብራል፥ የኃይል ፍቅር አጥንት ይሰብራል።
የሰውን ልጅ ማጥፋት እንጂ ማሸነፍ አትችልም። ሆድ የባሰውን ዳቦ ሰጥተህ ጠመንጃ ታስታጥቀዋለህ።
ፍትኃዊ የሃብት ክፍፍል፥ የአንድ መሃበረሰብን ስልጣኔ ማሳያ ቁልፍ መሳሪያ ነው።
መሸከም ከምትችለው በላይ ከምትሰበስብ መሸከም የምትችለውን ያህል ተሸክመህ ቶሎ አምልጥ።
ደካማ ሕዝብ ለወስላታ መንግስት አይስክሬም ነው፤ ወስላታ መንግስት ለደካማ ሕዝብ አስክሬን ነው።
84
ጊዜ ከሰጠኽው፥ ሁሉም ተለዋጭ ነው።
ያልተኖረ ህይወት የሞት ሞት ነው። አይደለም ስለማታውቀው፥ ስለምታውቀው ነገርም ቢሆን 100% እርግጠኛ መሆን አትችልም።
ጋን ውስጥ ያለሁ መብራት ነኝ፤ ከጋን ውስጥ ስወጣ ጨለምተኛ እሆናለሁ።
ከመወለድህ በፊት ማን ነበርክ? አሁንስ ማን ነህ? ከሞትክ ቡኋላስ ማን ትባላለህ?
የህዝብ ብዛት መጨመር ሃብታሙን ይበልጥ ያወፍረዋል፥ ድሃውን ያቀጭጨዋል።
ድሃ ባይጎሳቆል ሃብታም አይጠግብም ነበር።
85
እንስሶች ህመም አይሰማቸውም ብሎ ለሚያስብ፥ የእራሱን ብሽሽት ይመዝልግና ይሞክረው።
ሁሉም ሰው ባይዋሽ ኖሮማ እውነት እንደ አልማዝ ብርቅዬና ብርቅርቅ አትሆንም ነበር።
ከኖርክ አይቀር ነቅንቀኽው እለፍ! የበታችነት ስሜት እንዲሰማህ የሚያረግህ ሰው እውነተኛ ጠላትህ ነው።
ሳይበሳጩም መኖር ይቻላል! (ሰላም ለናፈቃቸው ወይም ካልተቆጡ ኦክሲጅን ለሚያጠራቸው ሰዎች)
ሰው በሰውነቱ ሊከበር በስራው ሊደነቅ ይገባዋል። ስለምግብ ብክለት ግድ የማይሰጠው መንግስት፥ ስለድምጽ ብክለት ብታወራለት አይገባውም።
የሸረሪቱን ድር ለማጥፋት ትንኞቹን ማጥፋት በቂ ነው።
86
ነጻነት ደስታ ነው፥ ሰላም ደስታ ነው፥ ጤንነት ደስታ ነው፥ ጥበብ ደስታ ነው።
መሳሳት ቀላል ነው፥ ስህተትን ማመን ግን ሊከብድ ይችላል።
ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ያደረገው አካል ጦርነቱን እንዳሸነፈ ይቆጠራል።
አሪፍ አወዳደቅ የሚያውቅ ብዙ አይጎዳም። እየፈለክ ከጠፈህ ፈላጊ አታጣም። ነገሩ ሚገባህ በጆሮህ ሳይሆን በልቦናህ ስታደምጠው ነው።
ይድረስ ለወታደር፥ ለአስተማሪ፥ ለገበሬና ለዶክተር፤ ክብር ለእናንተ ይሁን!
87
ብዙ ጨለምተኛ አትሁን፥ ብዙ ተስፈኛም አትሁን፤ ምክንያታዊና ሃቀኛ ሁን።
ገንዘብ ማለት የጥቂት ባለሃብቶች ደህንነት ማረጋገጫ ወረቀት፥ ለብዙኃኑ ደግሞ የባርነት ማህተም ነው።
99.9% እርግጠኛ ብትሆንም 100% እርግጠኛ አይደለህም። ወይም በቀላሉ፥ እርግጠኛ አይደለህም!
ትዝታ/ትውስታ ሲለካ፥ ጊዜ ነው ለካ! ሞት በጉቦ አይደለልም። (ለወስላታና ሞላጫ ሌቦች) አሁን አሁን እንኳ የኑሮ ውድነቱም እረከሰ። የእምነት ጥንካሬ ከፍቅር ይበልጣል። በእምነት ላይ መሰረት ያላደረገ ፍቅር ጊዜውን ጠብቆ መፈረካከሱ አይቀሬ ነው።
88
ህይወት ህልም ልትሆን አትችልም፤ እስከዛሬ ማን ባነንኩ ያለ አለ?
መሃበረሰቡ የተቀበለው ርኩስ ድርጊት፥ ለመሃበረሰቡ ግብረገባዊ ነው።
አምነህ የወደድከው፥ ወደህ ካመንከው የተሻለ ነው። የሰው ልጅ ጥያቄ ከዝግመታዊ ለውጡ ጋር፥ ከመሰልጠኑ በፊት፥ ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም? እየሰለጠነ ሲመጣ፥ መልካም ነው ወይስ መጥፎ ነው? ሲሰለጥን፥ ትክክል ነው ወይስ ትክክል አይደለም? ከሰለጠነ ቡኋላ፥ ይጠቅማል ወይስ አይጠቅምም?
89
ባርነት መልኩ ይለያይ እንጂ አሁንም በህይወት አለ። የሰው ዘር በጠቅላላ እኩል የስልጣኔ ደረጃ ላይ እሰካልደረሰ ድረስ ባርነት ህያው ሆኖ ይቀጥላል።
መናፈቅ ከመፈቀር ይበልጣል። ሰው ሲወድህ እራስህን መውደድ ትጀምራለህ፤ ሰው ሲጠላህ እራስህን መጥላት ትጀምራለህ።
እራስህን ከምታፈቅረው በላይ የሚያፈቅርህ ሰው ሲያጋጥምህ በፍቅር ትወድቃለህ።
በራሱ ዛቢያ የሚሽከረከር ሰው በማናቸውም ጎታች ኃይል ተጽእኖ ውስጥ ሊወድቅ አይችልም።
የመፈቃቀርና የመነፋፈቅ ስሜት የሚያንጸባርቅ ፍጥረት እንደ ሰው ሊቆጠር ይችላል።
ኃዘን ሲጋራ ይቀንሳል፥ ደስታ ሲካፈል ይባዛል።
90
ምድር ላይ ያሳረፍከው የጣት አሻራ እስካልጠፋ ድረስ ህያው ነህ፥ አልሞትክም።
በህይወት ሳለን ማፍቀር መፈቀር፥ ካለፍን ቡኃላ መታወስ አለመረሳት እንፈልጋለን። እኛ የሰው ልጆች ነን!
ትክክለኛ ዋጋውን፥ ስታጣው ታውቀዋለህ። ልብህ ውስጥ ያስቀመጥከው ሰው አይናፍቅህም። ሞት ባይኖር ህይወት አትጣፍጥም፥ ጨለማ ባይኖር ጨረቃ አትደምቅም፥ ክረምት ባይኖር ጸሃይ አትናፍቅም።
ባለማወቅ ስድብ ሆነው ለተሰዉ የአማርኛ ቃላት፦ ነፍስ ይማር።
የሰው መልካምነት እንጂ መጥፎነት የማይነገርበት ብቸኛ ቦታ ስርዓተ ቀብሩ ላይ ነው።
91
ከሞትኩ ቡኃላ ሰው ምን ይለኛል ብሎ ለሚጨነቅ ሰው ምን ትመክረዋለህ?
እድሜ ለመንግስት፥ ለውጥ ማምጣት እየቻሉ ሽባ ሆነው የቀሩ ስንት ዜጎች አፍርቷል!
ቢሪዮክራሲውን ካልቀበርከው የብልጽግና ትንሳኤ ይናፍቀሃል።
የህግ የበላይነት ናፍቆናል፥ የመንግስት የበላይነት ሰልችቶናል።
የመከራ ክትባት አልፎ አልፎ እጠቀማለሁ። በሰላም ጊዜ እራሴን አውቄ የስቃይ መርፌ እወጋዋለሁ።
የሳይካትሪ ሆስፒታል አልጋ ውስጥ መገላበጥ ካልፈለክ የሳይኮሎጂ መጸሃፍትን ማገላበጥ አማራጭ ሊሆን ይችላል።
ቆሻሻ አውጡዎች ቆሻሾች ሳይሆኑ ጽዳቶች ናቸው!
92
- “ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ መስራት አለብን!” - “በሳምንት ሰባት ቀን፥ ሌሊትን ጨምሮ መስራት ይጠበቅብናል!” - “በአመት 365 ቀን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳንል መስራት ይገባናል!” እነዚህና መሰል አባባሎች፥ 80% የተማረው የሰው ሃይል ተመርቆ ስራአጥ በሆነበት ሀገር የሚሰሩ አይመስለኝም።
ሃገራችን የሚያስፈልጋት ብዙ ሃቀኛ መሪዎች ሳይሆን ትንሽ ወስላታ መሪዎች ነው።
አንድ የማታውቀውን ሰው 100 ብር ይሰጥሃል ግደለው ተባልክ። ትገለዋለህ? ለምን?
አንድ የማታውቀውን ሰው 100 ቢሊየን ብር ይሰጥሃል ግደለው ተባልክ። ትገለዋለህ? ለምን?
ወንጀል ሲፈጸም አይተህ የአይን ምስክር ካልሆንክ የወንጀሉ ተባባሪ ነህ።
93
ስራ በሌለበት ሀገር ውስጥ ሰርቶ መብላት የማይችል ሰው ቢሰርቅ ይገርምሃል?
ሁልጊዜ ምትስቅበት ሰው አንዴ ተሳስቶ ከሳቀብህ፥ አሸነፈህ!
እራሴን ስፈትሽ አንተን አገኘሁት። የሰዎች ደስታ ለአንተ ሃሴት ሊሆን ይገባል። በራስህ ፍልስፍና እንጂ በማንም ፍልስፍና አትመራ። “እኔ ካልሞትኩ አንተ አጠግብም!” አለኝ። “አዎ፥ እኔ ካልሞትኩ አንተ አጠግብም!” ደገመው። “ማነህ አንተ?” ብዬ ጠየኩት። እሱም ጎርነን ባለ ድምጽ “መንግስቱ!” ብሎ መለሰልኝ።
አብረን ካልተራብን አብረን አንጠግብም። ሃሳብ ሲሰረቅ ኪስ ባዶ ይቀራል።
94
ለሰው ብለህ የሰረቅኽው፥ ለራስህ ብለህ ከሰረቅኽው ይበልጥ ፍትሃዊ ይመስላል።
እውቀትን ፈጠርነው ወይስ አገኘነው? ሃሳብህ እውን ከሆነ፥ ስትረሳው የት ይሄዳል? አንዳንዴ ህልሜ እውን ይሆንና ሲቀሰቅሱኝ እናደዳለሁ።
ለሁለተኛ ጊዜ እየኖርክ አለመሆኑን እንዴት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ?
ህሊና ውሸት ናት፥ እውነታው ከብዷታል። ነጻነትህ የተነጠቀው፥ ደህንነትህን ለመንግስት አደራ የሰጠህ ቀን ነው።
ስለፊትህ አትጨነቅ! ውስጥህ ካላበራ ፊትህ አይደምቅም።
95
የተወለድክበትን ቀን ባታውቀው፥ አሁን ያለህበትን እድሜ በትክክል መገመት ምትችል ይመስልሃል?
በከንቱ ያጠፋኽው ጊዜ የትኛው ነው? በደስታ ያጠፋኽው ወይስ በስራ ያጠፋኽው?
የሰው ልጅ አንድ ሚሆነው እኩል ሲጠግብ ነው። ኃይማኖት ባይኖር የሰው ልጅ እጣፈንታ ምን ይሆን ነበር?
ከሚሰጠው ጥቅም በላይ የሚቀበለው ካመዘነ፥ ሰውዬው ሌባ ነው!
ጥሩና መጥፎን የፈጠረው የሰው ልጅ እንጂ ተፈጥሮ አይደለም።
አንድ ዶሮ በ50 ሳንቲም የገዙት የ105 ዓመት አያቴ የዘንድሮውን የ1,000 ብር ዶሮ በተመሳሳይ አፍ እያጣጣሙት ነው።
96
ጨለማው ናፍቆኛል፥ የብርሃኑ ዘላለማዊነት አስተማማኝ አይደለም።
ትዳር ለዘልዛላ ሰው የእግር ካቴና ነው። ሁሉም ሰው በትላትሎች ፊት እኩል ነው። የሰው ልጅ በመሆኑ ያልተጸጸተ፥ ሰው አይደለም! ፈልግ ታገኛለህ፥ አግኝ በጣም ትፈልጋለህ፥ በጣም ፈልግ በጣም ታገኛለህ፥ በጣም አግኝ እጅግ በጣም ትፈልጋለህ ... (ይቀጥላል)
ጎጆ ሰርተን እንዳንኖር ሁላ ተከልክለናል፥ የወፎች አምላክ ይፋረደን!
የድሃና የሃብታም ፍላጎት አንድ ነው፤ ፍላጎታቸውን የሚያሳኩበት መንገድ ግን ሊለያይ ይችላል።
ብስለት ልዩነት ያጠባል።
97
ድሃ ሃብታም የሚሆነው ሲያር ነው፤ ሃብታም ድሃ የሚሆነው ሲበስል ነው።
አትክልት ተመጋቢ ነኝ ብለህ ከበሬ ቀንድ ማምለጥ አትችልም።
ሽንፈትን መቀበል የመሰለ አሸናፊነት የለም። የቤት ስራዬን ባለመስራቴ አትዘንብኝ፥ ቤት ስለሌለኝ ነው።
ስራ ያጣ ጋዜጠኛ ሴራ ይጎነጉናል። ወይ መብትህን ታስከብራለህ ወይ ታስረክባለህ። የአንዳንድ ትላልቅ የመንግስት ድርጅቶችን የደንበኛ አገልግሎት የስልክ መስመር ከመጠበቅ የምጸዓትን ቀን መጠባበቅ ይቀላል።
30 ዓመት ተምረህ 70 ዓመት መስራት ወይስ 70 ዓመት ተምረህ 30 ዓመት መስራት?
98
ትርምስ ብቻ! ሁሉም ነገር አንድ ነው። ምንም አዲስ ነገር አላየሁም!
ዓለም ፈጠረችህ፥ ዓለምኽን ፈጠርካት። እኩልነት እንደ በታችነት የሚታየው በሃብታም ዘንድ ነው።
ኢኮኖሚው ሲራብ ፖለቲካው ይጠግባል። አንድ ነገር እንድ ነው፤ ምንም ነገር ሁሉም ነገር ነው።
እድል ከሌለህ ፈጣሪህ አይሰማህም፤ እድል ካለህ ሳትለምነው በፊት ተሰምተኃል!
ጡጥ ... ማነው? በጭረቅረቅረቅረቅረቅረቅ ... (አንዳንዴ ምንነታቸው ሳይታወቅ ባሉበት ሁኔታ ቢቀመጡ የሚያምርባቸው ነገሮች አሉ።)
99
የደስታው ምንጭ ደርቋል፥ የመከራው ቀንበር ከብዷል፥ የሰማዩ ዝናብ ጠፍቷል፥ የገበሬው ማሳ ከስሟል፥ የዓለም ገበያ ተመናምኗል፥ የሰው አውሬነት አይሏል፥ የተስፋው ዓለም ጨልሟል፥ ስምንተኛው ሺ ተገባዷል፥ የምጽዓት ቀን ቀርቧል።
ግድግዳዬ ላይ ያለውን ትልቅ ሸረሪት ለመግደል ጫማዬን አውልቄ ቀና ብዬ ሳይ፥ ሸረሪቱ ቦታው ላይ የለም። ቤቴን ለቅቄ ወጣሁ።
ከቢንቢ የሌሊት ንዝነዛ ለማምለጥ ለቢንቢ ባንክ አንድ የደም ጠብታ በየቀኑ ለመለገስ ፈቃደኛ ነኝ።
100
“ሚሰራ ነገር ካለ ሚሰራ ነገር አለ ማለት ነው።” የእዚህን ዓረፍተ ነገር የሁለተኛው “ሚሰራ” የሚለው ፊደል ላይ ያለውን “ሰ” ማጥበቅ ፈለኩኝ፥ ግን አልቻልኩም። ካልጠበቀ ደግሞ ዓረፍተ ነገሩ አይሰራም።
ሁሌ የውኃ ብቻ! አንዳንዴም የገንዘቡ ቢዘንብ አሪፍ ነበር።
ፊቱ ሲያንጸባርቅ ማየት አማረኝ። በቃሪያ ጥፊ ወለወልኩት። አሁን ማንጸባረቅ ጀመረ።
ቫምፓየሩ የጻድቁን ሰውዬ አንገት ነከሰው። ቫምፓየሩ ነው ወደ ጻድቅ ሰው የሚለወጠው ወይስ ጻድቁ ሰው ወደ ቫምፓየሩ?
ጡንቻዬ ሲያለቅስ ላብ ይረግፈዋል። ለዓለማችን የውቅያኖስ ውኃ መጠን መጨመር የሰው ልጆች እንባ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
101
ስርዓትን ካላነገስከው ስርዓት አልበኝነት ይነግስብሃል።
እራስህን ከፍና ዝቅ እያደረክ “ሊሆን አይችልም!” እያልክ ተናገር። አሁን ደግሞ እራስህ ከቀኝ ወደ ግራ እየነቀነክ ሞክረው። የሁለተኛው አገላለጽ ለምን ትክክል ይመስላል?
ስራዬ እንኳን ብዙ አይከብድም፥ ወጪ ግን ይበዛዋል። በሳምንት 4 ቀን ሎተሪ ቆራጭ ነኝ።
ጥቁርና ነጭ ዓለም ውስጥ የሚኖርን ሰው ስለከለር ብታስረዳው አይገባውም።
ኢትዬጲስ ድምጽዋ ከተዘጋ ከአስረስ ጋር አይደለችም ማለት ነው።
እስከዛሬ ሁላችንም እድሜያችንን ተሳስተናል፤ በመሃጸን ውስጥ ያሳለፍነው 9 ወር የት ገባ?
102
ብጠቅሳት ብጠቅሳት ሊገባት አልቻለም። አንድ ዓይን እንዳለኝ ዘንግቼው ነበር።
አንድ አዞ የእውነት አዝኖ ቢያለቅስ አሁንም የአዞ እንባ ይባላል?
የሚያክምህ ሐኪም በመሃል ተዝለፍልፎ ቢወድቅ፥ እራስህን ለማዳን በመጀመሪያ ሐኪሙን መርዳት ይኖርበሃል።
እንስሳት ሁሌም እራሳቸውን በተጠንቀቅ ይጠብቃሉ፥ ነጻነት አላቸው። ሰዎች ደህንነታቸው ይጠበቃል፥ ነጻነት ግን የላቸውም።
የራስ ምታት መድኃኒት ለማዘዝ ባዶ እራቁትህን ካላየሁህ የሚል ዶክተር፥ እራሱ እራስ ምታት ነው።
ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም፤ ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበር፤ የኢንተርኔትም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር። ኢንተርኔትም፦ ብርሃን ይሁን አለ፤ ጎግልም ሆነ።
103
ፊትህን በመስታወት እያየኽው፥ “ጤና ይስጥልን?” ስትለው በዛኛው በኩል ምላሹ “አብሮ ይስጥልን” ቢሆን የአንተ ቀጣይ ምላሽ ምን ይሆናል?
ሁሉም ነገር ይቻላል እያሉ ሰውን ማሞኘት ምን ማለት ነው! ሁሉም ነገር አይቻልም! እንዲያውም ከሚቻለው ነገር የማይቻለው ያመዝናል። በእርግጥ መሞከሩ አይከፋም።
ሙሉ የአዕምሮ ንቅለተካላ አደረኩ፤ ቅራኔዬ ከተከለሰውነቴ ጋር መሆኑ አሁን ነው የገባኝ!
አለም አቀፍ የጦርነት ህግ እያለ፥ አለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድቤት ለምን አስፈለገ?
የሳይካትሪ መጻሃፍትን በማንበብ እራሴን አዝናናለሁ።
በራሴ አምናለሁ፥ በተስፈ ተስፈ ቆርጫለሁ።
104
የመሰማት ነጻነት ሳይኖርህ የመናገር ነጻነት ቢሰጥህ ምን ዋጋ አለው!
ስንት ህይወት ቀጥፌያለሁ መሰለህ! እነዛ ጥሩ መአዛ ያላቸው ዕጽዋት ትዝ ይሉኛል።
ከሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይልቅ ለእንስሳት መብት ተሟጋቾች የላቀ አክብሮት አለኝ። ደካሞች ሁሌም ሊታገዙ ይገባል!
ሰብአዊ መብትን የመጠበቅ የመጨረሻ ስልጣን (ሃላፊነት?) የተሰጠው አካል ማንነው? ይህ አካል ተጠሪነቱ ለማንነው? መብቱ ቢጣስ ለማንነው አቤት የሚለው?
ስልጣን እንደ ጀላቲ ይጣፍጣል፥ እንጨቱ እስከሚቀር መላስህን/ምላስህን አታቆምም።
ስአቱ ከሮጠብኝ፥ ከራሴ ጋር ነበርኩ ማለት ነው። ተይዛለች ባክህ። እሷን ያገባት ጋኔኑ ነው።
105
ሞኖፖሊ የለም ማለት ነጻ ገበያ አለ ማለት አይደለም።
ኩዋንተም ፊዚክስ ከአእምሮ በላይ ነው፥ አትረዳውም። የተረዳኽው ከመሰለህ፥ ከአእምሮህ በታች አሳንሰህዋል ማለት ነው።
እሾኽ ያለው ተክል መልእክቱ ይህ ነው፦ “ተጠንቀቁ፥ ወይ መድሃኒት ወይ መርዝ ነኝ”።
መግደል ህጋዊ ቢሆን፥ መኖር የሌለባቸው ሰዎች ብዛታቸው!
በቲቪ የሚታየው ጥብስ ሸተተኝ ካለህ፥ ቅድም ቀምሼው ወድጄዋለሁ በለው። (ውሸትን በውሸት አክሸፈው!)
ሰዎች አሁን ካልተረዱህ፥ ወይ የዛሬ ጀዝባ ወይ የነገ ጀግና ነህ።
እራሴን እየጠላሁ መሆኔን የማውቀው ሰውን መጥላት ስጀምር ነው።
106
ወፎች ሲጎራረሱ፥ የሰው ልጅ ሲባላ አየሁ። ጥንብአንሳ፥ ደሞዝ አልባ የጽዳት ሰራተኛ ነው። ደረጃ ሲጸዳ ከላይ ወደታች እንጂ ከታች ወደላይ አይደለም። ደረጃውን አንድ በአንድ ከታች ወደላይ የምታጸዳ ከሆነ፥ ሙሉ ለሙሉ አጽድተህ ለመጨረስ፥ የደረጃውን ብዛት ያህል ጊዜ መውጣትና መውረድ ሊኖርብህ ነው። (ሙስናን ለማጽዳት ከላይ እንጀምር!)
አቧራ የሚሰበስብ ምንጣፍ ገዛሁ፤ የአቧራ ማጽጃ ማሽን መግዛት አላስፈለገኝም።
የመጽሃፍ ሽታ ሱስ፥ የንባብ ሱሰኛ አድርጎኛል። ባለጌ ካልሆንክ የባለጌ ስድብ አይገባህም። ቁርስ እየበላሁ፥ ምሳ እያማረኝ፤ እራትን ሳስበው፥ አሁን ሞት አማረኝ።
107
የኮብል ስቶኑ ግብዓተ-መሬት በጭቃ ተደምድሟል። ምስል ዘላለማዊ ነው፥ አምሳል ጠፊ ነው። ዜሮ ቁጥር ያሳዝነኛል፤ አንድ ሚልዮን ብር ቢኖርህም ለዜሮ ማካፈል አትችልም። (1,000,000/0) ሒሳቡን ስራው።
ከአንድ ሰው ሁለቱ አዕምሮው ተምታቶበታል። የውኃ ቧንቧችን ዝምብላ ፈሷን እየፈሳች ትሄዳለች። ፍቅር፥ መደመር ሳይሆን መባዛት፤ ጥላቻ፥ መቀነስ ሳይሆን መጣፈት አለበት!
ያልተጸነሰ ልጅና ያልተጸነሰ ኃሳብ አይወለድም። ድብን ያለ እንቅልፍ ውስጥ ላለ ሰው አንድ ሰዓት እና ስምንት ሰዓት አንድ ናቸው። በህይወት ለሌለ ሰው አንድ ዓመት እና ስምንት ቢሊዮን ዓመት አንድ ናቸው።
108
ያችን የዋሽንት ድምጽ የተለያየ ሬድዬ ጣብያ ላይ በተመሳሳይ ሰዓት ከሰማሃት፥ ታዋቂ ሰው አርፏል ማለት ነው።
ልብስ በመሸጥ እተዳደራለሁ፥ ችግሩ ሁሉም ልብሶች የእኔ ናቸው።
የሽንት ቤት ሰልፍ ላይ የምትደንሰውን ዳንስ፥ ክለብ ውስጥ አትደግመውም።
በ 5 ደቂቃ የምትጨርሰውን ምግብ 5 ሰዓት ማዘጋጀት የለብህም።
ገንዘብ ማፍቀር አታቋርጥ፥ ገንዘቡ ሲያፈቅርህ ሃብታም ትሆናለህ።
ለውድቀት ትክክለኛው መንገድ ጥረት ነው፤ ለስኬት ትክክለኛው መንገድ ውድቀት ነው።
አስቀያሚው ፊትህን በፈገግታ ላጲስ አጥፈው።
109
እርሳስ ሲደንዝ መቅረጫ ያሾለዋል፤ ጭንቅላት ሲደንዝ መጽሃፍ ያሰላዋል።
ድሃ ነኝ፥ ግን የተትረፈረፈ ጊዜና ተሰፈ አለኝ። አንዳንድ ሰው 30 ዓመቱ ላይ ሞቶ 90ው ላይ ይቀበራል።
ብዙ ብር ማየት እጅ ያስቆረጥማል፤ ብዙ ብር መቁጠር ጣት ያስልሳል።
እውነት በድምጽ ፍጥነት፥ ውሸት በብርሃን ፍጥነት ይጓዛሉ።
ዝናብ ሲዘንብ አሪፍ ዘፋኝ ይወጣኛል፥ ማንም ሰው ስለማይሰማኝ በእራስ መተማመኔ ይጨምራል።
ገመዱ ደጋፊ፥ እንጨት ተደጋፊ? የኤሌክትሪክ ፖል !
110
ቲቪ ከማየት ሬድዮ መስማት፥ ሬድዮ ከመስማት መጽሃፍ ማንበብ፥ መጽሃፍ ከማንበብ እራስን ማዳማጥ የተሻለ ነው።
ሳቂታ ሰው ባለ 32 ኮከብ ሆቴል ባለቤት ነው። ጊዜ ይጥልሃል፥ መቃብር ያነሳሃል፤ ከመቃብር በታች ሁሉም ሰው እኩል ነው።
ወረኛ ሰውን በስልኩ ደረሰኝ ታውቀዋለህ። 1 ዓመት ስፖርት ከመከታተል፥ 1 ሰዓት መስራት። “እዚህ ግቢ ተናካሸ ውሻ አለ!”፦ ሌባውን ለማስፈራራት ወይስ ጤነኛውን ለማስጠንቀቅ?
የሃብታሞች መጸዳጃ ቦታ ላይ፦ “እዚህ አካባቢ መሽናት 100 ብር ያስቀጣል!”
ምግቡ እንዲጣፍጠኝ ከፈለክ እባክህ ክፈልልኝ?
111
የከበረ ድንጋይ በማንጠልጠል ለመከበር መሻት ድንጋይነት ነው።
የመሃል ጣትህን ከምትሰጠኝ የሌባ ጣትህን ስጠኝና እንታረቅ።
እኔ በዚህ ልቋጭ፥ መተንፈስ አማረኝ፤ ኢትዮጵያችን ትልማ፥ ጥሩ ጥሩ እንመኝ።
112
BACK COVER PAGE “አሁንም ተማሪ ነኝ፤ የዲግሪው ምርቃት ትምህርቴን እንዳደናቀፈው ተረድቻለሁ። ለተወሰኑ ጊዜያትም ቢሆን አዋቂ አስመስሎኛል፥ እኔም ሳላቀው መስያለሁ። ትምህርቱን አልቃወምም፥ ምርቃቱን ግን አልደግፍም። ሰዎች ስለራሳቸው ያላቸው ግምት ከወረቀት ጋር ከተዛመደ፥ የውስጥ እምቅ ሃይላቸውን ሊያዳፍነው ይችላል የሚል እምነት አለኝ። አዋቂ ማለት ትክክለኛ ትርጉሙ ባይገባኝም፥ ተማሪ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ግን በየቀኑ ይበልጥ እያወኩት ነው።” ኤፍሬም ዳንኤል
ዋጋ 99 ብር